“በዜጎች ላይ የሚደርሰው ጭፍጨፋ የተደጋገመው መንግሥት ችግር ፈቺ ምላሾችን ባለመስጠቱ ነው”-ኢዜማ
ጉዳዩ በቸልታ መታለፉ የችግሮቹ ምንጭ መንግስትና አካባቢውን የሚያስተዳድረው መዋቅሩ ነው ብሎ እንዲያምን መገደዱንም ገልጿል
ክልሉን በሚመሩት ኃላፊዎች ላይ ማጣራት ተደርጎ እርምጃ እንዲወሰድም ጠይቋል
“መንግሥት ችግር ፈቺ ምላሾችን ባለመስጠቱ በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰው ጭፍጨፋ ተደጋግሟል”-ኢዜማ
በመንግሥት በኩል የሚሰጡ ምላሾች ችግር ፈቺ ባለመሆናቸው ምክንያት በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰው ጭፍጨፋ መደጋገሙን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አስታወቀ፡፡
“የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማክበር እና ማስከበር ያልቻለ መንግሥት ስለ ልማት እና ብልፅግና የማውራት የሞራል ልዕልና ሊኖረው አይችልም” ሲል መግለጫ ያወጣው ፓርቲው ከሰሞኑ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን በግፍ በተገደሉ ዜጎች የተሰማውን ሃዘን ገልጿል፡፡
በክልሉ ላጋጠሙ ተደጋጋሚ ችግሮች የሚሰጡ ምላሾች ችግር ፈቺ አይደሉም ያለው ኢዜማ የችግሮቹ ምንጭ አካባቢውን የሚያስተዳድረው የመንግሥት መዋቅር እና ችግሩን በቸልታ እያየ ያለው የፌደራል መንግሥት ነው ብሎ እንዲያምን መገደዱን በመግለጫው አስታውቋል።
ከዚህ በፊት የተፈፀሙ ጥቃቶች አጥፊዎች እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አመራሮች ላይ ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ባለመወሰዳቸው ችግሩ አሁንም ስለመቀጠሉም ነው የገለጸው።
ክልሉን በሚመሩት ኃላፊዎች ላይ ማጣራት ተደርጎ እርምጃ ካልተወሰደ ግድያና ማፈናቀሉ ይቆማል ብሎ እንደማያምንም በመግለጫው አስቀምጧል።
የፌደራል መንግሥት እንደዚህ ዓይነቱ ጥቃቶች ከመድረሳቸው በፊት ለመከላከል እና በቶሎ ለማስቆም ከምንም ጉዳይ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባልም ነው ያለው፡፡
“የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር የዜጎችን በሕይወት መኖር ማክበር እና ማስከበር ነው” ያለም ሲሆን “ይሄን ማድረግ ያልቻለ መንግሥት ስለ ልማት እና ብልፅግና የማውራት የሞራል ልዕልና ሊኖረው” እንደማይችልም ገልጿል፡፡
ከሰሞኑ በክልሉ ተፈጸመ በተባለው ጥቃት ከ80 የሚልቁ ሰዎች ህይወት ማለፉን ያልተረጋገጡ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ጥቃቱ ማንነትን መሰረት አድርጎ መፈጸሙንም ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት፡፡
ከአሁን ቀደም በአካባቢው ተደጋግመው በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካቶች መገደላቸውና መፈናቀላቸው የሚታወስ ነው፡፡