ሳምሰንግ በ55 አመት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰራተኞቹ የስራ ማቆም አድማ መተውበታል
የኩባንያው ሰራተኞች ማህበር በስራ ማቆም አድማው 28 ሺህ ሰራተኞች እንደሚሳተፉ አስታውቋል
የደቡብ ኮሪያው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የሰራተኞቹን የደመወዝና ጉርሻ ጥያቄ ለመፍታት ቃል ገብቷል
በደቡብ ኮሪያ የሚገኙ የሳምንሰንግ ኩባንያ ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ ጀምረዋል።
በስራ ማቆም አድማው ከኩባንያው የደቡብ ኮሪያ ሰራተኞች ሩብ የሚሆኑት (28 ሺህ ገደማ) እንደሚሳተፉ የሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ማህበር አስታውቋል።
በኩባንያው የ55 አመት ታሪክ የመጀመሪያው ነው የተባለው የስራ ማቆም አድማ ዋነኛው ምክንያት የደመወዝ እና ጉርሻ ወይም ቦነስ ጥያቄ አለመመለሱ ነው ተብሏል።
የኩባንያው የሰራተኞች ማህበር ከአለማችን ቀዳሚው የስማርት ስልኮች አምራች ተቋም ጋር ሲያደርገው የነበረው ድርድር ውጤት ባለማምጣቱ ሰራተኞች በዛሬው እለት ፈቃድ ወጥተው ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ ማቅረቡን ሲኤንኤን ዘግቧል።
የማህበሩ ሊቀመንበር ሰን ወሞክ አብዛኞቹ ሰራተኞች አመታዊ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው የስራ ማቆም አድማውን መቀላቀላቸውን ያሳወቁ ሲሆን፥ በሴኡል በሚገኘው የተቋሙ መስሪያ ቤትም ሰራተኞች ተቃውሟቸውን ማሰማት መጀመራቸው ተዘግቧል።
“ሰራተኞችን አክብሩ! የ6 ነጥብ 5 ፐርሰንት የደመወዝ ጭማሪ ወይም የ200 ፐርሰንት ጉርሻ አይደለም ጥያቄያችን” ሲሉ መደመጣቸውንም ፍራንስ 24 አስነብቧል።
ለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ የሚውሉ ሚሞሪ ቺፕስ በማቅረብ ቁጥር አንድ የሆነው ሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ከጥር ወር ጀምሮ ከሰራተኞች ማህበሩ ጋር በደመወዝና አመታዊ ጉርሻ (ቦነስ) ሲያደርጉት የቆዩት ድርድር ስምምነት አልተደረሰበትም።
የተጀመረው የስራ ማቆም አድማም በኩባንያው ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ያለመ ነው ተብሏል።
የሳምሰንግ ቃልአቀባይ ግን ፈቃድ የወሰዱ ሰራተኞች ቁጥርን ባይጠቅሱም የስራ ማቆም አድማው በኩባንያው የእለት ተዕለት ስራ ላይ ምንም አይነት ጫና እንደማይፈጥር ነው የተናገሩት።
ከሰራተኛ ማህበሩ ጋር የተጀመረው ድርድር ቀጥሎ ቅሬታውን ለመስፋት እንደሚሰራም ቃል ገብተዋል።
የሳምሰንግ ግሩፕ እህት ኩባንያ የሆነው ሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እየገነነ መሄድ በስማርት ስልክም ሆነ በማይክሮ ቺፕ ገበያው ይበልጥ ተፈላፊነቱን ጨምረውለታል።
ባለፈው ወርም በ2024 የመጀመሪያ ሩብ አመት ገቢው በ10 እጥፍ ማደጉን መግለጹ የሚታወስ ነው።