የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት “በሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንደጸና ይቆያል” አሉ
ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን “ሞስኮከፍተኛ ዋጋ መክፈሉን መቀጠል አለባት” ማለታቸው አይዘነጋም
ፕሬዝዳንቷ ፤ የዩክሬን ጦርነት “በህግና በጠመንጃ የበላይነት መካከል የሚደረግ ጦርነት ነው” ብለዋል
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን በሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንደጸና የሚቆይ ይሆናል አሉ።
ፕሬዝዳንቷ ለአውሮፓ ፓርላማ በሳሙት ንግግር “ሩሲያ በዩክሬን ላይ ለፈጸመችው ወረራ ልትቀጣ ይገባል” ብለዋል።
በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት በህግ የበላይነት እና በጠመንጃ መካከል የሚደረግ ጦርነት ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ አውሮፓውያን በሞስኮ ላይ ያላቸውን ቁርጠኝነት መቀጠል አለባቸው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ቮን ደር ሌየን ፤ “በጣም ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ ማዕቀቡ እንደጸና የሚቆይ ይሆናል ፤አሁን ማረጋጋት ሳይሆን ቁርጠኝነትን የምናሳይበት ጊዜ ነው”ም ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ከሁለት ወራት በፊት ስድስት ሰፊ እና ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ማእቀቦች ውጤታማነት ለመጠበቅ እና ለማጠናከር አዳዲስ የማዕቀብ እርምጃዎች ለመሰውሰድ በሚያስችሉት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የጋራ ሃሳብ ላይ መድረሱ አይዘነጋም፡፡
በዚህም ህብረቱ፤ በሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ አዳዲስ ማዕቀቦች ተጨምረውበት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና እንዲራዘም ከሚል ውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን ፤ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገው ጦርነት እስከቀጠለችበት ህብረቱ በክሬምሊን ላይ የሚጥለው ማዕቀብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እንዲሁም የተጣለው ማዕቀብ እስከ ጥር 2023 እንዲራዘም ከውሳኔ መደረሱ በወቅቱ መናገራቸውም የሚታወስ ነው፡፡
ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን በወቅቱ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ “ሞስኮ ለጥቃቱ ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉን መቀጠል አለባት” ብለውም ነበር፡፡
አውሮፓውያን ይህን ይበሉ እንጂ ፤ የምዕራባውያን ማዕቀቦች እያዘነቡባት ያለችው ሩሲያ፤ “ዓላማዬን እስካሳካ ድረስ የሚቆም ወታደራዊ ዘመቻ የለም” ስትል እየተደመጠች ነው፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ከቀናት በፊት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻው መጀመሪያ ላይ የተቀመጡት አላማዎች እስኪሳኩ ድረስ ይቀጥላል" ብለዋል።
አሁን ላይ የሩሲያ አየር፣ ሮኬቶችና መድፍ ኃይሎች የኩፒያንስክ እና ኢዚዩም የከተማ ማዕከሎችን ጨምሮ በዩክሬን የጦር ኃይሎች ይዞታወች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት በመሰንዘር ላይ እንደሆኑም ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ ከኪቭ ጋር ሊኖሩ ስለሚችሉ የሰላም ንግግሮች ተጠይቀውም፤ በሞስኮ እና በኪቭ መካከል የሚደረጉ "የድርድር ተስፋዎች የሉም" የሚል ምላሽ መስጠታቸው ኤኤፍፒ ዘግቧል።