የአውሮፓ ህብረት የሩስያ ቱሪስቶችን ማገድ አለበት-የዩክሬን
የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በ“ቪዛ ጉዳይ” ለመምከር በቼክ ሪፓብሊኳ መዲና ፕራግ ከትመዋል
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፤ ቱሪስቶች ቪዛ መከልከል ሩሲያ ለጀመረችው የዘር ማጥፋት ጦርነት ተገቢ ምላሽ ይሆናል
የአውሮፓ ህብረት የሩስያ ቱሪስቶችን ማገድ አለበት ሲሉ የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ አሳሰቡ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በጉዳዩ ላይ የተለያየ ሀሳብ አንጸባርቀዋል የተባሉትን የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በቼክ ሪፐብሊክ ፕራግ ለውይይት በተቀመጡበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡
በፕራግ እየተካሄደ ባለው ስብሰባ የምስራቅ ኖርዲክ ሀገራት ሩሲያውያን ቱሪስቶች ሙሉ በሙሉ ቪዛ እንዲከለከሉ የሚል ምክር ሃሰብ ሲያቀርቡ ፤ በተቃራኒው ጀርመንና ፈረንሳይ “የሩሲያ ቱሪስቶችን ቪዛ ለመከልከል የቀረበውን ምክረ ሃሳብ” ተቃውሞውታል፡፡
ሀገራቱ ባወጡት የፍራንኮ-ጀርመን ሰነድ እንዳመላከቱት “የአውሮፓ ህብረት የሩስያ ቱሪስቶችን አውሮፓን ከመጎብኘት ሊከለክል አይገባም” ብለዋል።
"በዚህ አውድ ውስጥ የአንዳንድ አባል ሀገራትን ስጋት የምንረዳ ቢሆንም፤ በዴሞክራሲያዊ ስርአት ውስጥ ህይወትን የመኖርና የማጣጠም ትርጉም አቅልለን ማየት የለብንም" ሲሉም አክለዋል።
“የእኛ የቪዛ ፖሊሲዎች ማንጸባረቅ ያለባቸው ከሩሲያ መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት ሳይሆን ከሩሲያ ዜጎች ጋር ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ነው” ብለዋል ሀገራቱ ባወጡት ሰነድ።
የጀርመንና ፈረንሳይ ሃሳብ ግን በዩክሬን በኩል የተወደደ አይመስልም፡፡
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኩሌባ፤ ውጤት ማምጣት ሚቻለው በሩሲያውያን ላይ ጠንካራና ወጥነት ያለው ፖሊሲ ተግባራዊ ሲደረግ ብቻ መሆኑ መነገራቸውም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
"በሩሲያውያን ቱሪስቶችና አንዳንድ አካላት ላይ የሚደረገው የቪዛ እገዳ ሩሲያ በአውሮፓ እምብርት ላይ ለጀመረችው የዘር ማጥፋት ጦርነት ተገቢ ምላሽ ይሆናል"ም ነው ያሉት ኩሌባ።
እስካሁን በላው መረጃ እንደ ኢስቶኒያ ፣ ፊንላንድ ፣ ሊቱዌኒያ ፣ ላቲቪያ እና ፖላንድ የመሳሰሉ ሀገራት “የሩሲያ ዜጎች ወደ አውሮፓ ህብረት እና ወደ ሼንገን አካባቢ የሚያደርጉት ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ይገባል” የሚል የጋራ መግለጫ ማውጣታቸው እንዲሁም የተለያዩ እርምጃዎች መውሰድ መጀመራቸው ታውቋል።