ሩሲያ የተጣሉባት ማዕቀቦች ካልተነሱ ወደ አውሮፓ ነዳጅ እንደማትልክ ገለጸች
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦችን ጥለዋል
የቡድን ሰባት አባል ሀገራት በሩሲያ ነዳጅ ላይ የዋጋ ተመን ማውጣታቸው ይታወሳል
ሩሲያ የተጣሉባት ማዕቀቦች የማይነሱ ከሆነ ወደ አውሮፓ ነዳጅ እንደማትልክ ገልጻለች።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ስድስት ወራት ያለፈው ሲሆን ጦርነቱ በዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዲመዘገብ ምክንያት ሆኗል።
ጦርነቱ በዓለም ዲፕሎማሲ ላይ የተለያዩ መፋለሶችን ያስከተለ ሲሆን ሀገራት ከትብብር ይልቅ ጎራ ለይተው እንዲሰለፉ እያደረገም ይገኛል።
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ላይ በተለያየ መንገድ በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ በሩሲያ ላይ ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦችን ጥለዋል።
ሩሲያም የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ስትሆን ማዕቀቡ ለአውሮፓ ሀገራት የምታቀርበውን ጋዝ ሽያጭ እክል አስከትሏል።
ይሄንን ተከትሎም 40 በመቶ ለሚሆኑ የአውሮፓ ሀገራት ነዳጅ ስታቀርብ የነበረችው ሩሲያ በማዕቀቡ ምክንያት ለአውሮፓውያን ነዳጅ መላክ አለመቻሏን በተደጋጋሚ ገልጻለች።
በነዳጅ ዕጥረት እየተፈተነ ያለው የአውሮፓ ህብረትም በሩሲያ ላይ የጣለውን ማእቀብ እስከማላላት ቢደርስም በሩሲያ ላይ የተጣሉት ሁሉም ማዕቀቦች እስካልተነሱ ድረስ ሩሲያ ምንም አይነት ነዳጅ እንደማትልክ ራሺያ ቱዴይ ዘግቧል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የአውሮፓ ሀገራት እና ኩባንያዎች በሩሲያ ላይ የጣሉት ማዕቀብ ሳይነሳ አንዲት ጠብታ ነዳጅ አንልክም ሲሉ ተናግረዋል።
የአውሮፓ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆኑት ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ብሪታንያ፣ ቤልጂየም እና ሌሎች ሀገራት በነዳጅ ዕጥረት እየተፈተኑ ናቸው ተብሏል።
እነዚህ ሀገራት ሩሲያ ነዳጇን እንደጦር መሳሪያ እየተጠቀመችበት ነው ሲሉም ሞስኮን ከሰዋል።
የዓለማችን ሰባቱ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆኑት የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ከሰሞኑ በሩሲያ ነዳጅ ላይ የዋጋ ተመን ማውጣታቸው ይታወሳል።
እነዚህ ሀገራት ሩሲያ ነዳጇን በተተመነላት ዋጋ መሰረት ለአውሮፓ ሀገራት እንድትሸጥ የወሰኑ ቢሆንም ሩሲያ በበኩሏ ምንም አይነት ነዳጅ ወደ አውሮፓ አልሸጥም የሚል ውሳኔ አሳልፋለች።