በብራዚል በደረሰ የአውሮፕላን አደጋ የ61 ሰዎች ህይወት አለፈ
57 ተጓዞችን 4 የበረራ ሰራተኞችን ይዞ ሲጓዝ በነበረው አውሮፕላን ከካስካቫል ከተማ ወደ ሳኦ ፖሎ እየተጓዘ ባለበት ነው አደጋው ያጋጠመው
በማህበራዊ ትስስር ገጾች በመዘዋወር ላይ የሚገኙ ተንቀሳቃሽ ምስሎች አውሮፕላኑ ከሰማይ ቁልቁል እየተሸከረከረ ሲምዘገዘግ አሳይተዋል
በብራዚል ሳኦ ፖሎ በደረሰ የአውሮፕላን አደጋ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ የሁሉም ተሳፋሪዎች ህይወት አለፏል፡፡
57 ተጓዞችን እና 4 የበረራ ሰራተኞችን ይዞ በሀገር ውስጥ በረራ ከካስካቫል ከተማ ወደ ሳኦፖሎ ጉዞ ሲያደርግ የነበረው አውሮፕላን በሰሜናዊ ሳኦ ፖሎ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ተከስክሷል፡፡
በተከሰከሰው አውሮፕላን ላይ ለመሳፈር ትኬት ቆርጠው የነበሩ ሁለት ተጓዞች በሰአት መዘግየት በረራው አልምልጧቸው ከአደጋው ተርፈዋል፡፡
በመኖርያ ኮኖዶሚኒየም ህንጻ ላይ የተከሰከሰው አውሮፕላን ከተጓዞቹ ባለፈ በወደቀበት ስፍራ ላይ በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት አላደረስም፡፡
ኤቲአር 72-500 የተባለው የመንገደኞች አውሮፕላን አምራች ኩባንያ የአደጋው መንስኤን ለማጣራት ከሀገሪቱ የሲቪል አቭየሽን ባለስልጣን ጋር በትብበር እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡
የሀገሪቱ የሲቭል አቭየሽን ባለስልጣን በበኩሉ አውሮፕላኑ በ2010 የተመረተ እና በጥሩ የአገልግሎት አቋም ላይ የሚገኝ እንደነበር ይፋ አድርጓል፡፡
በተጨማሪም የአውሮፕላኑን መረጃ የሚመዘግበው ጥቁር ሳጥን አደጋው ከደረሰበት ስፍራ መገኝቱን ገልጾ በቀጣይ የምርመራ ውጤቶችን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ነው ያስታወቀው፡፡
የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉላ ዳሲልቫ በደረሰው አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች ሀዘናቸውን ሲገልጹ የሳኦ ፖሎ ግዛት አስተዳደር ደግሞ የሶስት ቀናት የሚቆይ ሀዘን አውጇል፡፡
ብራዚል ከዚህ ቀደም አሰከፊ የሚባል አደጋ የደረሰባት በ2007 ሲሆን በዚሁ በሳኦ ፖሎ ግዛት ባጋጠመው አደጋ የ199 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡
በጣሊያን እና ፈረንሳይ ባለቤትነት በኤር ባስ ስር የሚገኝው ኤቲአር 72 የተባለው አውሮፕላን በ1994 በህንድ ባጋጠመው አደጋ 68 ሰዎች ሲሆን በኔፓል እና በኖርዌይም ተመሳሳይ አደጋን አስተናግዷል፡፡