በቢሾፍቱ የአውሮፕላን አደጋ ተጎጂ ቤተሰቦች የስቃይ እና ህመም ካሳ እንዲከፈላቸው ጠየቁ
የአሜሪካ ፍርድ ቤት በአውሮፕላኑ አደጋ የሞቱ ሰዎች ላጋጠማቸው ሕመም ቤተሰቦቻቸው ቦይንግን መክሰስ እንደሚችሉ ተገልጿል
ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ከአራት ዓመት በፊት ተከስክሶ ለ157 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል
የአሜሪካ ፍርድ ቤት በኢትዮጵያ አውሮፕላን አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ተጎጂ ቤተሰቦች ተጨማሪ ክስ እንዲከሱ ፈቀደ፡፡
መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ ናይሮቢ በመብረር ላይ እያለ ባጋጠመው የመከስከስ አደጋ የ157 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።
መነሻውን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ መዳረሻውን ደግሞ ወደ ኬንያ ናይሮቢ ጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አድርጎ በረራ የጀመረው ET-302 መሬት በለቀቀ በ6ኛው ደቂቃ ላይ ቢሾፍቱ ልዩ ስፍራው ቱሉ ፎራ በተባለ ቦታ ነበር የተከሰከሰው።
በዚህ አደጋ የበረራ አስተናጋጆቹን ጨምሮ ሁሉም ተሳፋሪዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን የአደጋው መነሻ የአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ባጠናው የምርመራ ሪፖርት ማስታወቁ ይታወሳል።
ቦይንግ ኩባንያ መጀመሪያ ላይ ለአደጋው ሃላፊነት እንደማይወስድ የገለጸ ቢሆንም ዘግይቶ ግን ኩባንያው ጥፋቱን በማመን ለተፈጠረው አደጋ ሀላፊነት እንደሚወስድ ገልጿል።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር የአደጋው የተጠቃለለ ሪፖርቱ ላይ እንደጠቀሰው የቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን “ከቁጥጥር ውጪ” እንዲሆን እና አደጋው እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው፤ “ኤምካስ” (Maneuvering Characteristics Augmentation System – MCAS) በተሰኘው የአውሮፕላኑ የመቆጣጠሪያ ስርዓት ላይ በነበረ ችግር ነው፡፡
ይህን ተከትሎም የአደጋው ተጎጂ ቤተሰቦች ከዚህ በፊት ቦይንግ ኩባንያን የከሰሱ ሲሆን አሁን ደግሞ ተጨማሪ ክስ በአውሮፕላኑ አምራች ኩባንያ ላይ መመስረት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ የአደጋው ተጎጂ ቤተሰቦች ቦይንግ ኩባንያን ተጎጂዎች ለደረሰባቸው ሕመም መክሰስ እንደሚችሉ የአሜሪካ ፍርድ ቤት ፈቅዷል፡፡
በአሜሪካ ኢሊዮንስ ግዛት ዳኛ የሖኔት ጆርጅ አሎንሶ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ላስተናገዱት ህመም እና ስቃይ ካሳ ለማግኘት ቦይንግን መክሰስ እንደሚችሉ መፍቀዳቸው በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
በዚህ አደጋ መክንያት ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች መካከል ዘጠኙ ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ 32ቱ ኬንያዊያን፣ 18ቱ ካናዳዊያን፣ 8ቱ ቻይናዊያን፣ 7ቱ ፈረንሳውያን፣ 6ቱ ከግብጽ፣ 5ቱ ከሆላንድ እንዲሁም 4ቱ ከህንድ እንደሆኑ በወቅቱ መገለጹ ይታወሳል፡፡