የአረብ ሀገራት በጋዛ ተኩስ እንዲቆም ጥሪ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል
ሳኡዲ አረቢያ የእስራኤልና ሃማስ ጦርነትን ለማስቆም ያለሙ ሶስት ጉባኤዎችን ለማስተናገድ መዘጋጀቷን አስታወቀች።
የሀገሪቱ ኢንቨስትመንት ሚኒስትር ካሊድ አል ፋሊህ እንዳስታወቁት፥ ሪያድ የፊታችን ቅዳሜ የአረብ ሀገራት ጉባኤን ታስተናግዳለች።
ከዚህ ጉባኤ አንድ ቀን በኋላም የእስላሚክ ትብብር ድርጅት በጋዛ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ አስቸኳይ ጉባኤውን በሪያድ ያደርጋል ነው ያሉት።
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ እሁድ በሚጀመረው ጉባኤ ላይ እንደሚሳተፉ መገለጹን ሬውተርስ ዘግቧል።
ኢራን እና ሳኡዲ በመጋቢት ወር በቻይና አደራዳሪነት ግንኙነታቸውን ለማደስ መስማማታቸው የሚታወስ ነው።
የፍልስጤሙን ሃማስ እና የሊባኖሱን ሄዝቦላህ ትደግፋለች የምትባለው ቴህራን በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ውስጥ የአሜሪካ ጣልቃገብነት ጦርነቱን ወደቀጠናው እንዳያስፋፋው ያሰጋል ብላለች።
ዋሽንግተን ግዙፍ የጦር መርከቦቿንና ከ2 ሺህ በላይ ተጨማሪ ወታደሮቿን ወደ መካከለኛው ምስራቅ መላኳም ውጥረቱን አባብሶታል።
ኢራንና የተለያዩ የአረብ ሀገራት ከ10 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን የቀጠፈው ጦርነት እንዲቆም ያቀረቡት ጥሪ በአሜሪካና እስራኤል ተቀባይነት አላገኘም።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በጋዛ ተኩስ እንዲቆም ማድረግ ሃማስን ዳግም እንዲደራጅና በእስራኤል ላይ ጥቃት እንዲከፍት እድል መፍጠር ነው ማለታቸው ይታወሳል።
በጋዛ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው ያለችው ሳኡዲ አረቢያም ጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲበጅለት ሶስት አስቸኳይ ጉባኤዎችን በቀናት ልዩነት ለማድረግ መዘጋጀቷን ገልጻለች።
የፊታችን ቅዳሜ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የአረብ - አፍሪካ ጉባኤም ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።