ሳኡዲ ከአሜሪካ ጋር በምትፈጽመው የመከላከያ ስምምነት ከእስራኤል ጋር ለመታረቅ የጀመረችውን ሂደት አቋረጠች
ሪያድ ከእስራኤል ጋር አዲስ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከመጀመሩ በፊት ለፍልስጤም የሀገርነት እውቅና እንዲሰጥ ጠይቃለች
ንጉሳዊ አስተዳደሩ ከአሜሪካ ጋር በሚፈጽመው ወታደራዊ ስምምነት በአረብ ሀገራት እጅ የማይገኙ አሜሪካ ሰራሽ የጦር መሳርያዎች እንደሚሸጥለት ቃል ተገብቶለታል
ሳኡዲ ረብያ ከአሜሪካ ጋር በምታደርገው የመከላከያ ስምምነት ከእስራኤል ጋር ግንኙነቷን ለማደስ ጀምራው የነበረውን ሂደት አቋረጠች፡፡
የአረቡን አለም ከእስራኤል ጋር ለማስታረቅ እና ግንኙነትን ለማደስ በተጀመረው ሂደት “ጨዋታ ቀያሪ” ነው የሚባለው የቴልአቪቭ እና የሪያድ እርቅ በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች ሲካሄዱበት ቆይተዋል፡፡
የአሜሪካ ሴኔት በአረቡ ሀገራት እጅ የማይገኙ ከፍተኛ የጦር መሳርያዎችን ለባሕረሰላጤው ሀገር ለመሸጥ የቀረበውን የመከላከያ ስምምነት ለማጸደቅ ከእስራኤል ጋር እርቅ መፈጸምን በቅድመ ሁኔታነት አቅርቧል፡፡
ይህ ስምምነት ሪያድ ከምታገኝው የጦር መሳርያ ሽያጭ ባለፈ ከአሜሪካ ጋር የመከላከያ አጋርነትን እና የጋራ ወታደራዊ ልምምድን ያጠቃልላል፡፡
ከዚህ ቀደም ንጉሳዊ አስተዳደሩ እስራኤል የሁለት ሀገርነት እውቅናን በይፋ የምታውጅ ከሆነ ግንኙነቱን ለማደስ ፈቃደኛ መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡
ነገር ግን እስራኤል በጋዛ ላይ እያደረሰች በምትገኝው ወታደራዊ ጥቃት ምክንያት በሳውዲ አረቢያ እና በሰፊው የመካከለኛው ምስራቅ ህዝብ የተቀሰቀሰውን ቁጣ ተከትሎ ይህ አቋሟ መቀየሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ልዑል አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን የፍልስጤምን ሀገርነት ለማረጋገጥ ድጋሚ የሀገርነት እውቅና ቅድመ ሁኔታን አስቀምጠዋል።
በዚህ የተነሳም አሜሪካ ሁለቱን ሀገራት ሊያቀራርብ የሚችል ነገር ግን ቀድሞ ከነበረው የመከላከያ ስምምነት አነስ ያለ የወታደራዊ የትብብር ሰነድን ገቢራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ መሆኗ ተሰምቷል፡፡
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀያል ሀገር ጋር የሚደረግን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደ ከፍተኛ ስኬት ፣ በአረቡ አለምም ሰፊ ተቀባይነትን ለማግኝት መንገድ ጠራጊ እንደሆነ ያምናሉ፡፡
ሆኖም የፍልስጤምን ሀገርነት በሚያረጋግጥ ሂደት ላይ የሚፈጸም የትኛውም ስምምነት ጥምር መንግስታቸውን ሊያፈርስ ስለሚችል ጉዳዩን በጥንቃቄ ለመምራት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ዲፕሎማቶች ይናገራሉ፡፡
ሮይተርስ በምንጭነት የተቀሳቸው የአሜሪካ ዲፕሎማቶች እንደሚሉት ከእስራኤል እና ሳኡዲ አዲስ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተግበራዊ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ሁለቱም መሪዎች በቀጠናው እና በሀገር ውስጥ በሚገጥማቸው ተቃውሞ ተሸብበው ባሉበት ወቅት፤ ሪያድ እና ዋሽንግተን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጥር ወር ከዋይት ኃውስ ከመውጣታቸው በፊት መጠነኛ የሆነ የመከላከያ ስምምነት ተግባራዊ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡
ከቀደመው የመከላከያ ትብብር አነስ ያለ እንደሆነ የተነገረለት ስምምነት በዋናነት ከኢራን የሚመጡ አካባቢያዊ ስጋቶችን በጋራ ለመከላከል ፣ በአሜሪካ እና በሳኡዲ የመከላከያ ድርጅቶች መካከል ያለውን ትብብር ለማሳደግ እንዲሁም ሪያድ ለመሳርያ ግዢ ወደ ቻይና እንዳታማትር ለመከላከል ያግዛል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ሳኡዲ በተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች በተለይም በድሮን ምርት ላይ የምታደርገውን ጥረት መደገፍ ፣ የስልጠና፣ ሎጅስቲክስ እና የሳይበር ደህንነት ድጋፍን አሜሪካ የምታደርግ ይሆናል፡፡
የሚሳኤል መከላከያን እና የተቀናጀ መከላከያን ለማጠናከር “የፓትሪዮት” ሚሳኤል ሻለቃን በባሕረሰላጤው ሀገር ልታሰማራ ትችላለች።
ነገር ግን የውጭ ጥቃት በሚደርስበት ጊዜ የአሜሪካ ጦር የዓለምን ትልቁን ዘይት ላኪ እንዲጠብቅ የሚያስገድድ የጋራ መከላከያ ስምምነት አይሆንም።
በዚህ ሂደት ውስጥ የባይደን አስተዳደር እስራኤል የሁለት ሀገርነት መፍትሄን እንድትቀበል ፣ ሳኡዲ አረብያ ደግሞ ከሙሉ የሀገርነት አውቅና ቅድመ ሁኔታ ተለሳልሳ በሁለት ሀገርነት መፍትሄ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት እንዲጀምሩ ለማሳምን እንደሚጥር ይጠበቃል፡፡