የሲ.አይ.ኤ ዳይሬክተር ዊሊያም በርንስ ወደ ሪያድ አቅንተው ለሳዑዲ አረቢያ ስሞታ አቅርበዋል ብሏል
የመካከለኛው ምስራቅ የበላይነትን ለመቆጣጠር ፍጥጫ ውስጥ የነበሩት ሳውዲ አረቢያ እና ኢራን በቻይና አደራዳሪነት ወደ ስምምነት መምጣታቸው ይታወሳል።
ሁለቱ ሀገራት በደረሱበት ስምምነት መሰረት ኤምባሲዎቻቸውን ለመክፈት፣ የቀጥታ በረራ ለመጀመር፣ የመሪዎች እና ባለሃብቶች ጉብኝት እንዲኖርም ተስማምተዋል።
ለዓመታት የእጅ አዙር ጦርነት ውስጥ የነበሩት ሳዑዲ አረቢያ እና ኢራን በዋሸንግተን ተገዳዳሪ በሆነችው ቻይና አደራዳሪነት መስማማታቸው ለዋሸንግተን ምቾት እንዳልሰጠ ተገልጿል።
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳድርም የሀገሪቱ ስለላ ዋና ሃላፊ ዊሊያም በርንስን ወደ ሪያድ በመላክ ከልዑል አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ጋር መወያየታቸውን ዎልስትሪት ጆርናል ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ሳውዲ አረቢያ እያደረገች ያለው ግንኙነት አሜሪካን ቅር ማሰኘቱን እና የመከዳት ስሜት እንደተሰማት ለልዑል ሳልማን ነግረዋቸዋል ተብሏል።
አሜሪካ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር በመተባበር ከዚህ በፊት በኢራን እና ሶሪያ ላይ ማዕቀቦችን የጣለች ሲሆን ሳዑዲ አረቢያ ከሀገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት በማደስ ላይ ትገኛለች።
የሶሪያወን ፕሬዝዳንት የፊታችን ግንቦት በአረብ ሊግ ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ ለመጋበዝ መወሰኗንም አስታውቃለች።
የሳዑዲ አረቢያ ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ሬሲ ሪያድን እንዲጎበኙ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ፕሬዝዳንቱም ግብዣውን መቀበላቸው ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም በየመን በእጅ አዙር እየተዋጉ ያሉት ኢራን እና ሳዑዲ አረቢያ ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ውይይት በቅርቡ እንደሚጀምሩም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ከዚህ በተጨማሪም ሳዑዲ አረቢያ ዕለታዊ የነዳጅ ምርት መጠንን ከሩሲያ እና ሌሎች ሀገራት ጋር በመመካከር በቀን አንድ ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ለመቀነስ መስማማቷ ዋሸንግተንን እንዳላስደሰተ ተገልጿል።
የሳዑዲ የሀይል ሚኒስተር ልዑል አብዱላዚዝ ቢን ሳልማን ከሰሞኑ ከብዙ ሀገራት ከእኛ ጋር ናችሁ? ወይስ ጀርባችሁን ሰጥታችሁናል? የሚሉ ጥያቄዎች ለሀገራቸው እየቀረበ መሆኑን ነገር ግን እኛ ከሳውዲ አረቢያ ዜጎች ጋር ብቻ ነን ብለዋል።