ሳዑዲ አረቢያ ለ700 ሴት ጠበቆች የስራ ፈቃድ ሰጠች
ሳዑዲ አቢያ በፈረንጆቹ 2018 ነበር ሴቶች ከቤት ውጭ ያሉ ስራዎችን መስራት እንዲችሉ የፈቀደችው
አዲሱ ፈቃድ የህግ ባለሞያ ሴቶችን ቁጥር ወደ ሁለት ሽህ 100 ከፍ እንዲል ያደርጋል
ሳዑዲ አረቢያ 700 ሴት ጠበቆች የስራ ፈቃድ መስጠቷን አስታውቃለች።
ሀገሪቱ የሴቶችን መብት ለማሳደግ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው።
ሳዑዲ አረቢያ 700 ለሚሆኑ ሴት የህግ ባለሞያዎች ተጨማሪ እድል ለመፍጠር ባለመው እቅዷ መሰረት አዲስ ፈቃድ መስጠቷን አስታውቃለች።
የሳዑዲ ፍትሕ ሚንስቴር ወሰድኩት ባለው እርምጃ በሀገሪቱ የጥብቅና ፈቃድ ያላቸውን የህግ ባለሞያ ሴቶች ቁጥርን ወደ ሁለት ሽህ 100 ከፍ አድርጓል።
ፈቃዱ ሴቶች የህግ ባለሞያዎች እንዲበራከቱ ያደርጋል ተብሎለታል። የጄዳ ጠበቃ የሆኑት ሳፋ ኦምራን ለናሽናል ኒውስ እንዳሉት ፈቃዱ “የሴቶችን የሕግ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚረዳ ከመሆኑም በላይ ወጣቱን ትውልድ በእጅጉ ያነሳሳል” ብለዋል።
ጠበቆች ወደ ፍትህ ሚንስቴር መሄድ ሳይጠበቅባቸው በበይነ መረብ በማመልከትና ስልጠና በመውሰድ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ ተብሏል።
ሀገሪቱ በፈረንጆቹ 2018 ነበር ሴቶች ከቤት ውጭ ያሉ ስራዎችን መስራት፣ መንጃ ፈቃድ ማውጣት፣ ለብቻ መኖር እና ካለ ወንዶች አጀባ መንቀሳቀስን የመሰሉ የእኩልነት ውሳኔዎችን ያሳለፈቸው።
ሳዑዲ አረቢያ በፈረንጆቹ 2030 በያዘችው ራዕይ ሴቶች በሁሉም የማሕበረሰብ ዘርፍ አበርክቶ እንዲኖራቸው እንዲሁም በስራ ገበያው እንዲሳተፉ ለማድረግ የማሻሻያ ስራ እየሰራች ነው።
ባለፉት አምስት ዓመታትም ስራ ያላቸው ሴቶች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩ ተነግሯል። በ35 በመቶ አድጓል የተባለው የሴቶች የስራ ተሳርፎ በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው ተብሏል።