በአዲሱ የኢራን ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት ላይ የተገኙት የዩኤኢ የመቻቻልና አብሮነት ሚኒስትር ከፕሬዝዳንት ረዒሲ ጋር ተወያዩ
በዩኤኢ የመቻቻልና አብሮነት ሚኒስትር ሼክ ናህያን የተመራው ልኡክ ወደ ቴህራን አቅንቷል
በውይይቱ አዲሱ የኢራን ፕሬዝዳንት ሀገራቸው ከዩኤኢ ጋር ያላትን ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት እንዳለት ገልጸዋል
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) የመቻቻልና አብሮነት ሚኒስትር ሼክ ናህያን ቢን ሙባረክ አል-ናህያን ከአዲሱ የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ረዒሲ ጋር መገናኘታቸው ተሰማ፡፡
ሚኒስትሩ ሼክ ናህያን ልኡክ መርተው ወደ ቴህራን አቅንተዋል፡፡
ሚኒሰትሩ ለአዲሱ የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ረዒሲ ከፕሬዝዳንት ሼክ ከሊፋ፣ከምክትል ፕሬዝዳንትና የዱባዩ ገዥ ሼክ መሀመድ ቢን ራሺድ እንዲሁም ከአቡዳቢ አልጋ ወራሽ እና የዩኤኢ ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ የተላከላቸው የሰላምታ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ሼክ ናህያን ከኢራኑ ፕሬዝዳንት ራይሲ ጋር በሁለቱዮሽ ጉዳዮች ላይ እንደመከሩም ነው የኤሜሬቱ ዜና አግልግሎት/WAM/ ዘገባ ሚያመለክተው፡፡
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ረዒሲ ሀገራቸው ከዩኤኢ ጋር በሁሉም መስኮች የምታደርገውን ግንኙነት የማጠናከር ጥልቅ ፍላጎት እንዳለት ለሚኒስትሩ መግለጻቸውን የዘገበው ደግሞ የኢራኑ እስላማዊት ሪፓብሊክ ዜና አገልግሎት (IRNA) ነው፡፡
የአቋም ሰው መሆናቸው የሚነገርላቸው የ60 ዓመቱ ረዒሲ ባለፈው ሰኔ ወር የተካሄደውን ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ሃሰን ሩሃኒን ተክተው የፕሬዚዳንትነት በትረ ስልጣን እንደጨበጡ የሚታወቅ ነው።
ፕሬዝዳንት ረዒሲ ቀጣይ የኢራናውያንን ተስፋ ብሩህ እንዲሆን የሀገሪቱ ፓርላማ እንዲተባበር እንደፈረንጆቹ ሃምሌ 27 መጠየቃቸውም እንዲሁ የሚታወስ ነው፡፡
“በሀገሪቱ የወደፊት እጣፈንታ በጣም ተስፋ አደርጋለሁ እናም ችግሮችን እና ውስንነቶችን ማሸነፍ እንደሚቻል እምነት አለኝ”ም ነበር ያሉት ፕሬዝዳንት ረዒሲ።
ሆኖም ዛሬ እሁድ ያቀርቡታል ተብሎ የነበረውን የአዳዲስ የካቢኔ አባላቶቻቸውን ዝርዝር አጠናቀው ለማቅረብ አለመቻላቸውን ነው አል ዐይን አረብኛ የዘገበው፡፡