ሰዎቹ በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው ነው የተረሸኑት
ሳዑዲ አረቢያ በአንድ ቀን 81 ሰዎችን ረሸነች፡፡
ሳዑዲ በሽብርተኝነት የጠረጠረቻቸው 81 ሰዎችን መረሻኗን ያስታወቀች ሲሆን ከተረሸኑት ሰዎች መካከልም ሰባቱ የመናዊያን እና ሶሪያዊያን ናቸው ተብሏል፡፡
81ዱ ሰዎች በሞት የተቀጡት በሳውዲ አረቢያ የሽብር አደጋ ለመፍጠር የጦር መሳሪያዎችን ሲያጓጉዙ እና አደጋ ለማድረስ ሲያሴሩ ተጠርጥረው ነው፡፡ የሽብርርኝነት ክስ የተመሰረተባቸው ነበሩም ተብሏል፡፡
ከተረሸኑት ሰዎች መካከል የአልቃይዳ እና የእስላሚክ ስቴት (አይ ኤስ) የሽብር ቡድን አባላት እንዳሉበት የአገሪቱ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው እንዲረሸኑ በአገሪቱ ፍርድ ቤት ተወስኖባቸዋል ሲልም ነው ሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ የዘገበው፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ታዋቂውን ጸሃፊ ራይፍ በዳዊን ከእስር በመልቀቋ ተመስግና የነበረችው ሳውዲ አረቢያ በአንድ ቀን 81 ሰዎችን መረሸኗ ትክክል አለመሆኑን የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች በመናገር ላይ ናቸው፡፡