ኢራን በኒውክሌር መርሐ ግብሯ ዙሪያ “ቁም ነገር አዘል”ድርድርን እንድታደርግ ሳዑዲ ጥሪ አቀረበች
ናታንዝ የተሰኘው የኢራን የኒውክሌር ተቋም ከሰሞኑ በኤሌክትሪክ ኃይል ቋቶቹ ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ እንዳጋጠመው የሚታወስ ነው
ኢራን ከወትሮው በተለየ መልኩ ከፍተኛ ጥራት ያለው ዩራኒዬምን ማበልጸግ እጀምራለሁ ማለቷ ሪያድን አስግቷል
ከኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ጋር የተያያዘውን ሰሞንኛ ጉዳይ በአይነ ቁራኛ እየተከታተለችው እንደሆነ ሳዑዲ አረቢያ አስታወቀች፡፡
በጉዳዩ “መስጋቷን” የገለጸችው ሪያድ “ሊፈጠር የሚችለውን ቀጣናዊ ውጥረት ለማርገብ”ቴህራን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር “ቁም ነገር አዘል ድርድሮችን እንድታደርግ” በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ጥሪ አቅርባለች፡፡
ሳዑዲ ይህን ያለችው ኢራን ከወትሮው በተለየ መልኩ ከፍተኛ ጥራት ያለው ዩራኒዬምን ማበልጸግ እንደምትጀምር ፕሬዝዳንቷ ሃሰን ሮሃኒ ማስታወቃቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ናታንዝ የተሰኘው የኢራን የኒውክሌር ተቋም ከሰሞኑ በኤሌክትሪክ ኃይል ቋቶቹ ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ አጋጥሞታል፡፡
“ከፍንዳታው ጀርባ እስራኤል አለች” በሚልም ነው ኢራን ከፍተኛ ጥራት ያለውን ዩራኒዬም እንደምታበለጽግ ያስታወቀችው፡፡
“አሁን ካለው የ20 በመቶ የጥራት ደረጃ የተሻለ እና የ60 በመቶ የጥራት ደረጃ ያለው ዩራኒዬምን አበለጽጋለሁ”ም ብላለች ቴህራን፡፡
ተጨማሪ 1,000 አዳዲስ የኒውክሌር ማብለያ መሳሪያዎችን (ሴንትሪፊዩሶችን) በናታንዝ እንደምትተክልም ነው ያስታወቀችው፡፡
ይህን ተከትሎም ሳዑዲ “ቴህራን ሊፈጠር የሚችለውን ውጥረት በማርገብ የቀጠናውን ሰላምና መረጋጋት ለበለጠ ውጥረት ከመዳረግ እንድትቆጠብ” ጥሪ አቅርባለች፡፡
በኦስትሪያ ቬና የተጀመረው ድርድር አስፈላጊነትንም ሪያድ በአጽንኦት ገልጻለች፡፡
ኢራን ድርድሮቹን “በቁም ነገርነት ይዛ” እንድትሳተፍም ጠይቃለች፡፡
ሆኖም “በድርድሮቹ ሊደረስ የሚቻልበት የትኛውም ዐይነት ስምምነት ቴህራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን እንድትታጠቅ ወይም ጦር መሳሪያዎቹን ለመታጠቅ ከምትችልበት ደረጃ ለመድረስ የማያስችል መሆን አለበት” ነው ሪያድ ያለችው፡፡
የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን ለመታጠቅ 90 በመቶ ያህል ጥራት ያለው ዩራኒምን ማበልጸግ እንደሚጠይቅ የ ዘ ናሽናል ዘገባ ያመለክታል፡፡