ሳውዲ አረቢያ በአሜሪካ የተቋቋመው የቀይ ባህር ዘብ ጥምረትን እንደማትቀላቀል ተገለጸ
አሜሪካ የቀይ ባህርን ከአደጋ ለመጠበቅ የተላያዩ ሀገራትን ያሳተፈ ቡድን አዋቅሬያለሁ ማለቷ ይታወሳል
የየመን አማጺያን ከእስራኤል በተጨማሪ የአሜሪካ መርከቦችን እንመታለን ሲሉ ዝተዋል
ሳውዲ አረቢያ በአሜሪካ የተቋቋመውን የቀይ ባህር ዘብ ጥምረትን እንደማትቀላቀል ተገለጸ፡፡
ለፍልስጤም ነጻነት እታገላለሁ የሚለው ሐማስ ከ80 ቀናት በፊት በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ጦርነት መቀስቀሱ ይታወሳል።
እስራኤል በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ከ20 ሺህ በላይ ፍልስጥኤማውያን ሲገደሉ ከ1ሺህ 200 በላይ እስራኤላውያንም ተገድለዋል።
የእስራኤልን የጋዛ ጥቃት ተከትሎ በርካታ ሀገራት እና ተቋማት ያወገዙ ሲሆን የየመኑ ሁቲ ታጣቂ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ባላቸው መርከቦች ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ ነው።
የሁቲን ጥቃት ተከትሎ የቀይ ባህር ትራንስፖርት አደጋ ላይ የወደቀ ሲሆን ይህን የዓለም ንግድ መሳለጫ መስመር ከአደጋ ለመጠበቅ በአሜሪካ የሚመራ የባህር ሀይል ጥበቃ ቡድን ይሰማራል ተብሏል።
በአሜሪካ ይፋ የተደረገውን ይህን የሀገራት ጥምረት በርካታ ሀገራት እንደሚቀላቀሉ የገለጹ ሲሆን ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ግሪክ፣ ኔዘርላንድ እና ስፔን ዋነኞቹ ናቸው።
ይሁንና የቀይ ባህር ትራንስፖርት ቅርብ የሆኑት ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የአሜሪካንን ጥምረት እንዳልተቀላቀሉ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ ሁለቱ ሀገራት በአሜሪካ አስተባባሪነት ይፋ የተደረገው የቀይ ባህር ጥበቃ ጥምረትን ያልተቀላቀሉት ለዓመታት የዘለቀው የየመን ጦርነት እንዳያገረሽ፣ ከኢራን ጋር በቅርቡ የጀመሩት መልካም ግንኙነት እንዳይበላሽ እና በመጀመሪያ እስራኤል የጋዛ ጦርነትን እንድታቆም ስለሚፈልጉ ነው ተብሏል፡፡
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከሳውዲ አረቢያ ይባረር ይሆን?
የየመን ሁቲ አማጺያን በበኩሉ እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን ጥቃት ካላቆመች በቀይ ባህር ላይ ጥቃት ማድረሱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
እንዲሁም የእስራኤል ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ የአሜሪካ መርከቦችን ማጥቃት እጀምራለሁ ሲልም አማጺያኑ አስታውቋል፡፡
የሁቲ አማጺያን ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን መርከቦች በሚሳኤል እና ሰው አልባ አውሮፕላን ማጥቃቱን ተከትሎ በርካታ የዓለማችን የሎጅስቲክስ ድርጅቶች በቀይ ባህር መጓዝ በማቆም ላይ ናቸው፡፡