ሳውዲ አረቢያ ሁለት ወታደሮቿን በሞት ቀጣች
ጥፋተኛ የተባሉት ወታደሮች አንገታቸው መቀላቱ ተገልጿል
ወታደሮቹ የሞት ፍርድ የተፈጸመባቸው በሀገር ክህደት ወንጀል ምክንያት ነው ተብሏል
ሳውዲ አረቢያ ሁለት ወታደሮቿን በሞት ቀጣች፡፡
የመካከለኛው ምስራቋ ሳውዲ አረቢያ በሀገር ክህደት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል በተባሉ ሁለት ወታደሮቿን በሞት ቀጥታለች፡፡
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ሌተናንት ኮለኔል ማጂድ ቢን ሙሳ አዋድ እና ቺፍ ስረጊንት የሱፍ ቢን ረዳ ሃሰን አል አዙኒ የሀገር ክህደት ወንጀል በመፈጸማቸው አንገታቸው ተቀልቶ ተገድለዋል ብሏል፡፡
ሚኒስተሩ አክሎም በሁለቱ ወታደሮች ላይ በተደረገው ማጣራት ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው እና ጥፋታቸውን ማስተባበል ባለመቻላቸው ፍርዱ መፈጸሙ ተገልጿል፡፡
ወታደሮቹ የተሰጣቸውን ሳውዲ አረቢያን ከማናቸውም ጉዳቶች የመጠበቅ ሃላፊነትን አልተወጡም በሚል በቀረበባቸው የሀገር ክህደት ወንጀል ክስ ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋልም ተብሏል፡፡
ባለፉት 4 ዓመታት ውስጥ 400 ሺህ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊያን ከሳውዲ አረቢያ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል
የሀገሪቱ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሆነው በተገኙት ሁለት ወታደሮች ላይ የሞት ፍርድ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን የተላለፈው ፍርድ መፈጸሙ ተገልጿል፡፡
ይሁንና ጥፋተኛ የተባሉት እና የሞት ፍርድ የተፈጸመባቸው ሁለት ወታደሮች ወንጀሉን መቼ እና የት እንደፈጸሙት አልተገለጸም፡፡
ሳውዲ አረቢያ የሞት ፍርድ በተላለፈባቸው ዜጎች ላይ ፍርዱን የምትፈጽመው አንገታቸውን በሰይፍ በመቅላት እንደሆነ የሀገሪቱ ህገ መንግስት ያስረዳል፡፡