ትራምፕ "በአፋጣኝ" ድርድር እንዲጀመር ከፕሬዝደንት ፑቲን ጋር መስማማታቸውን አስታወቁ
ሁለቱ መሪዎች አንዳቸው የሌላኛቸውን ሀገር ለመጎብኘት እንደተስማሙም ትራምፕ ተናግረዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/12/243-232512-download_700x400.jpeg)
ትራምፕ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም የሚያስፈልጉ ቅድም ሁኔታዎች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ አልጠቀሱም
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ "በአፋጣኝ" ድርድር እንዲጀመር ከፕሬዝደንት ፑቲን ጋር መስማማታቸውን አስታወቁ።
ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በዛሬው እለት ባደረጉት የ1:30 ደቂቃ የስልክ ንግግር ሶስት አመት ገደማ ያስቆጠረውን የዩክሬኑን ጦርነት ለማቆም ከዩክሬኑ መሪ ጋር "በአፋጣኝ" ድርድር እንዲጀመር መስማማታቸውን አስታውቀዋል።
ሁለቱ መሪዎች አንዳቸው የሌላኛቸውን ሀገር ለመጎብኘት እንደተስማሙም ትራምፕ ተናግረዋል።
ድርድሩን "ያደረግነውን ንግግር ለዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በማሳወቅ እንጀምራለን፤ "ይህን አሁን አደርገዋለሁ ሲሉ ፕሬዝደንት ትራምፕ ትሩዝ በተባለው የማህበራዊ ሚዲያቸው ገልጸዋል።
ትራምፕ አክለውም "የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ የሲአይኤ ኃላፊ ጆን ራትክሊፌ፣ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚካአል ዋልዝ፣ አምባሳደርና ልዩ መልእክተኛ ስቴቭ ዊክቶፍ ስኬታማ ይሆናል ብዩ የማምነውን ድርድር እንዲመሩ እየተጠየኩ ነው" ብለዋል።
ትራምፕ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም የሚያስፈልጉ ቅድም ሁኔታዎች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ አልጠቀሱም። ነገርግን የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፔቴ ሄግዘ የዩክሬን የኔቶ አባልነት ጉዳይ የማይሳካ መሆኑን ተናግረዋል።
ሄግዘ "አሜሪካ የዩክሬን የኔቶ አባልነት የስምምነቱ ውጤት ይሆናል ብላ አታምንም" ብለዋል።
የፕሬዝደንት ትራምፕ ከፍተኛ የታጋች ተደራዳሪ በሩሲያ ታሰሮ የነበረው አሜሪካዊ መምህር ማርክ ፎጌል እንዲፈታ ትራምፕ ከሩሲያው መሪ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሷል።
"ማርክ ፎጌልን ማስፈታት ወሳኝ ነበር፤ በዚህ ረገድ ሩሲያውያን በጣም፣ በጣም ተባባሪ ነበሩ" ሲሉ ዊትኮፍ በኋይት ሀውስ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
የፎጌል መለቀቅ የፕሬዝደንት ትራምፕና ፑቲን ግንኙነት ወደፊት እየጠነከረ የሚሄድ መሆኑን የሚያሳይ ነው ያሉት ዋትኮፍ "መልካም ግንኙነት ነበራቸው ብየ አስባለሁ"፤ ይህም መቀጠል አለበት ብለዋል። ፕሬዝደንት ትራምፕ ፎጌልን በኋይትሀውስ ተቀብለውታል።
ፎጌል ለጀርባ ህመሙ በህክምና የታዘዘ ማሪዋና ይዞ በመገኘቱ ከ2021 ጀምሮ በእስር ላይ ነበር። ፎጌልን በመልቀሏ ሩሲያን እንደሚያደንቁ የተናገሩት ትራምፕ "በጣም ፍትሃዊ" ከማለታቸው ውጭ ከሩሲያ ጋር የደረሱትን ስምምነት ዝርዝር ግልጽ አላደረጉም።
ፕሬዝደንት ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት አሸንፈው ቢሮ ከገቡ የዩክሬን- ሩሲያ ጦርነትን እንደሚያስቆሙ ቃል ገብተው ነበር።
ዩክሬን ድርድር ለመጀመር የሩሲያ ኃይሎች ከግዛቷ ጠቅልለው መውጣት አለባቸው የሚል ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣ የነበረ ሲሆን ሩሲያ ደግሞ የጦርነቱ የሚቆመው ዩክሬን የተፈጠረውን አዲስ የግዛት ለውጥ ከተቀበለችና ኔቶ የመግባት እቅዷን ከተወች ብቻ ነው ብላ ነበር።
በተጨማሪም ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ስምምነት ላይ ከመድረሷ በፊት የሰላም አስከባሪ እንዲሰፍርና ከአሜሪካ የደህንነት ዋስትና እንዲሰጣት እንደምትፈልግ ገልጻለች።