የሳዑዲ ልዑል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ከጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ግድያ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቱርክን ጎበኙ
ጉብኝቱ ሻክሮ ነበረው የአንካራ-ሪያድ የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያድስ ነው ተብሎለታል
የቱርክ ባለስልጣናት በዚህ ጉብኝት በኃይል፣ ኢኮኖሚ እና ደህንነት ላይ ያተኮሩ ስምምነቶች ይፈረማሉ እያሉ ነው
የሳዑዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ከፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር ለመነጋገር ከዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቱርክ ተጉዘዋል።
ጉብኝቱ እንደፈረንጆቹ በ2018 የሳዑዲ አረቢያ ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጊ በሳውዲ ቆንስላ ውስጥ ከተገደለ በኋላ ሻክሮ የነበረውን ሀገራቱ ግንኙነት ወደ ክፈተኛ ደረጃ ለማድረስ የተደረገ የመጀመሪያ ጉዞ ነው ተብሏል።
እስካሁን በይፋ የወጡ መረጃዎች ባይኖሩም፤ የቱርኩ ፕሬዝዳንት የሳዑዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማንን በአንካራ በሚገኘው ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግስት ተቀብለው የሚያነጋግሯቸው ይሆናል፡፡
ጉብኝቱ ሳዑዲው አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን በግብፅ እና በዮርዳኖስ ካደረጉት ጉብኝት የቀጠለ መሆኑም ነው የተገለጸው።
አንድ ከፍተኛ የቱርክ ባለስልጣን ለሮይተርስ እንደተናገሩት መሪዎቹ በሚያደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት "ሙሉውን መደበኛነት እና የቅድመ-ቀውስ ጊዜን ወደነበረበት መመለስ" ይጠበቃል ብለዋል ።
"አዲስ ዘመን ይጀምራል" ሲሉም አክለዋል ባለስልጣኑ።
እንደፈርነጆቹ በጥቅምት 2018 ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጊ በሳዑዲ ከተገደለ በኋላ በአንካራ እና በሪያድ መካከል ያለው ግንኙነት እምብዛም እንዳልሆነ ይታወቃል።
ኤርዶጋን በወቅቱ የሳዑዲ መንግስትን በ"ከፍተኛ ደረጃ" ተጠያቂ ማድረጋቸው አይዘነጋም።
መሀመድ ቢን ሳልማን በበኩላቸው በግድያው ውስጥ ምንም አይነት ተሳትፎ እንደሌላቸው በወቅቱ መናገራቸውም እንዲሁ ሚታወስ ነው።
ሆኖም ግንኙነታቸውን ለማስተካከል ለወራት ከፈጀ ጉዞ በኋላ አንካራ የግድያ ምርመራና የፍርድ ሂደት በሚያዝያ ወር ማቆሟንና በሳዑዲ ጥያቄ መሰረት ችሎቱ ወደ ሪያል ማዛወሯ ይታወሳል።
ይሁን እንጅ የአንካራና የሪያል ስምምነት ውሳኔ በወቅቱ በበርካታ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የተወገዘ ነበር፡፡
ምክንያቱም ደግሞ፤ ድርጀቶቹ ሳዑዲ አረቢያ ፍትሃዊ የፍርድ ሂደት ታደርጋለች ብለው እንደማይጠብቁ ሲገልጹ ነበር፡፡
መሀመድ ቢን ሳልማን ፤ የሳዑዲ አረቢያን ሰፊ ሀብት እና ዘይት የማምረት አቅም ከሰብአዊ መብት አያያዝ ጋር ተያይዞ የሚሰነዘርባውን ትችት ለማለዘብ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል።
ኤርዶጋንም እንደፈረንጆቹ በ2023 ከሚጠበቀው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በፊት የቱርክን ኢኮኖሚ ለማቃለል የሚረዳ የገንዘብ ድጋፍ ይፈልጋሉ።
እናም የአሁኑ ጉብኝት ሀገራቱ የጋራ ፍላጎቶች ከማሟላት ረገድ ጥሩ ፋይዳ አለው ተብሎ ይታመናል፡፡
የቱርክ ባለስልጣናት በዚህ ጉብኝት በሃይል፣ ኢኮኖሚ እና ደህንነት ላይ ያተኮሩ ስምምነቶች እንደሚፈረሙና የሳዑዲ ገንዘቦች በቱርክ የካፒታል ገበያ እንዲገቡ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
የሳዑዲ አረቢያው ልዑል አልጋወራሽ መሃመድ ቢን ሳልማን በትናንትናው ማክሰኞ እለት ካይሮን መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡
ቢን ሳልማን እና ፕሬዝዳንት ሲሲ በአል ኢትሃዲያ ቤተ መንግስት ተገናኝተው በሁለትዮሽ እና ሌሎች ቀጣናዊ ጉዳዮች መምከራቸውም ይታወቃል።
ሳዑዲ እና ግብጽ ለዘመናት የዘለቀና የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።
103 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ግብጽ ከሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ ለከፋ የስንዴ እጦት በተዳረገችበት በአሁኑ ወቅት እንኳን፤ ሳዑዲ በግብጽ ማዕከላዊ ባንክ የሚቀመጥ የ5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓ ይታወሳል።