መሃመድ ቢን ሳልማን ዮርዳኖስን እና ቱርክን ይጎበኛሉም ተብሏል
የሳዑዲ አረቢያው ልዑል አልጋወራሽ መሃመድ ቢን ሳልማን ትናንት ሰኞ ለሁለት ቀናት ጉብኝት ግብጽ ካይሮ ገብተዋል፡፡
ልዑል አልጋ ወራሹ ዮርዳኖስን እና ቱርክን ላካተተው ቀጣናዊ ጉብኝት ነው ግብጽ የገቡት፡፡
ካይሮ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በደረሱ ጊዜም የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሃገሪቱ ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ቢን ሳልማን እና ፕሬዝዳንት ሲሲ ዛሬ ማክሰኞ በአል ኢትሃዲያ ቤተ መንግስት ተገናኝተው በሁለትዮሽ እና ሌሎች ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡
ምክክሩ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት በመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ባሳረፈው ተጽዕኖ እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በቀጣይ ወር በሳዑዲ አረቢያ ለማድረግ ካሰቡት ጉብኝት ላይ ሊያተኩር እንደሚችል ሳዑዲ ፕሬዝ ዘግቧል፡፡
ባይደን በቅርቡ ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት ወደ ቀጣዩ ወር የመጀመሪያ ሳምንት አካባቢ ማዘዋወራቸው ይታወሳል፡፡
መሃመድ ቢን ሳልማን በነዳጅና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ስለሚጠበቀው የባይደን ጉብኝት ከቀጣናው መሪዎች ጋር ለመምከር በማሰብ ወደ ካይሮ ማቅናታቸውም ነው የተነገረው፡፡
ሳዑዲ እና ግብጽ የጠበቀ ግንኙነት አላቸው፡፡ 103 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ግብጽ ከሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ ለከፋ የስንዴ እጦት በተዳረገችበት በአሁኑ ወቅት እንኳን ሳዑዲ በግብጽ ማዕከላዊ ባንክ የሚቀመጥ የ5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓ ይታወሳል፡፡
ልዑል አልጋ ወራሹ በቀጣይ ዮርዳኖስን እና ቱርክን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል፡፡ ሳዑዲ ከቱርክ ጋር ያላት ግንኙነት በተለይም ከኳታር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መቋረጥ በኋላ ሻክሮ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡
ከሰሞኑ “ለሳዑዲ ህዝብ እሴቶች የማይመጥን ቀለም አላቸው” የተባሉ ቁሳቁሶችን ያስወገደችው ሳዑዲ በኢትዮጵያ፣ ቱርክ እና ህንድ ላይ ጥላው የነበረውን የጉዞ እገዳ ማንሳቷ ይታወሳል፡፡