ሳዑዲ አረቢያ የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን ማስተናገድ እንደምትፈልግ አስታወቀች
የሳዑዲ ስፖርት ሚኒስትር ልዑል አብዱልአዚዝ “ ኦሎምፒክ ለኛ ትልቁ ግብ ይሆናል” ብለዋል
ሳዑዲ “ስፖርትን ለገጽታ ግንባታ ታውለዋለች” የሚል ክስ ሲቀርብባት መስማት የተለመደ ነው
ከነዳጅ አምራች ኢንዱስትሪ በዘለለ ኢኮኖሚዋን ለማስፋት አቅዳ በመንቀሳቀስ ላይ የምትገኘው ሳዑዲ አረቢያ የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን የማተናገድ ትልቅ ፍላጎት እንዳላት አስታወቀች።
በዚህም የሀገሪቱ መንግስት በ2030 ለማሳካት ካቀዳቸው ዋና ዋና ፕሮጀክቶች አንዱ በስፖርት ላይ መዋዕለ ነዋይ ፈሰስ በማድረግ ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ የሚል እንደሆነም ተገልጿል።
ሳዑዲ አረቢያ በሚቀጥለው ዓመት የዓለም የቦክስና ካራቴ ያካተቱ የተለያዩ ጨዋታዎች ውድድር (World Combat Games) እንዲሁም የ2034ቱ የእስያ ጨዋታዎች ውድድር ለማዘጋጀት እንቅስቀሴ ትገኛለች።
የሳዑዲ አረቢያ ስፖርት ሚኒስትር ልዑል አብዱልአዚዝ ቢን ቱርኪ አል ፋይሰል በጅዳ እየተካሄዱ ባሉ የእስያ ጨዋታዎች መድረክ እንደተናገሩት "አሁን ዋናው ትኩረታችን የ2034 [የእስያ ጨዋታዎች] ነው፤ ነገር ግን ለወደፊቱ ከዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር ለመወያየት ዝግጁ ነን" ሲሉ ተደምጠዋል።
ሳዑዲ አረቢያ እንደዚህ አይነት ዝግጅቶችን ማስተናገድ እንደምንችል ያሳየች ይመስለኛልም ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
“በእርግጠኝነት፣ ኦሎምፒክ ለኛ ትልቁ ግብ ይሆናል” ብለዋል።
ሳዑዲ ሁንተናዊ እድገት እያስመዘገበች ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ "እውነታዎቹ እንደሚያሳዩት እነዚህን ዝግጅቶች ማስተናገድ ህዝባችንን ሆነ በሳዑዲ ውስጥ እየመጡ ያሉትን ለውጦች የሚጠቅም ነው" ሲሉም ተናግረዋል።