ሟቹን የኢራን ፕሬዝዳንት የሚተኩት መሱድ ፔዝሽኪያን ማን ናቸው?
በሄሊኮፕተር አደጋ ህይወታቸውን ያጡትን ኢብራሂም ራይሲን ለመተካት በተካሄደው ምርጫ ፔዝሽኪያን አሸንፈዋል
የአያቶላዎቹን ጥብቅ ሀይማኖታዊ አስተዳደርን እውቅና እሰጣለሁ የሚሉት ፔዝሽኪያን በኢራን ማህበረሰባዊ ነጻነትን አሰፍናለሁ ብለዋል
በለዘብተኛ አቋማቸው የሚታወቁት የ69 አመቱ የልብ ቀዶ ጥገና ሀኪም ከ30 ሚሊየን መራጭ 16 ሚሊየን ድምጽ በማግኝት አዲሱ የኢራን ፕሬዝዳንት ሆነዋል፡፡
ከ1979ኙ የኢራን አብዮት በኋላ ዝቅተኛ ቁጥር ያለው መራጭ በተሳተፈበት ውጥረት በተሞላበት ምርጫ ብቅ ያሉት ፕሬዝዳንት ብዙ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡
ውልደታቸው በመስከረም 29፣ 1954 በሰሜን ምዕራብ ኢራን ክፍል ማሃባድ ከተማ ነው፡፡ አዜሪ ከተሰኘው አናሳ ጎሳ ከተገኙ አባታቸው እና ከኩርድሽ እናታቸው የተወለዱት ፕሬዝዳንቱ በኢራቅ እና ኢራን ጦርነት ተሳታፊ ነበሩ፡፡
በጦርነቱ የህክምና ባለሙያዎችን ወደ ስፍራው በማሰማራት ጉዳት የደረሰባቸውን ኢራናውያን ወታደሮች ህክምናን እንዲያገኙ ብርቱ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ይነገርላቸዋል፡፡
የልብ ቀዶ ጥገና ሀኪም ከሆኑ በኋላ የታብሪዝ ዩኒቨርስቲ የሜዲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡
ሀዘን እና መሰበርን በቅጡ የሚያውቁት ፔዝሽኪያን በ1994 ባለቤታቸውን እና ሴት ልጃቸውን በመኪና አደጋ ካጡ በኋላ አንድ ሴት እና ሁለት ወንድ ልጆቻቸውን እስከዛሬ ሚስት ሳያገቡ ለብቻቸው አሳድገዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ የፖለቲካ ጉዟቸውን አንድ ሲሉ የሀገሪቱ ምክትል የጤና ሚንስትር በመሆን ነበር። ቀጥሎም በፕሬዝዳንት ሞሀመድ ካታሚ የስልጣን ዘመን የጤና ሚንስትር በመሆን አገልግለዋል፡፡
ከወግ አጥባቂ እና ሪፎርሚስት ከሚባሉ የኢራን ፖለቲከኞች ጋር በመሟገት የፖለቲካ ጊዜያቸውን ያሳለፉት ፕሬዝዳንቱ በለዘብተኛ አቋማቸው ይታወቃሉ፡፡
በ2006 ታብሪዝን በመወከል ወደ ፓርላማ ከገቡ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ምክትል አፈጉባኤ ሆነው ኢራንን ለማሻሻል ከሚጥሩ ፖለቲከኞች ጋር በትብብር ይሰሩ ነበር፡፡
ፔዝሽኪያን ምንም እንኳን በገለልተኛ እና ለዘብተኛ አቋማቸው ቢታወቁም ለኢራን አብዮታዩ ዘብ ጠባቂ ያላቸውን ክብር በተለያየ ጊዜ በይፋ ይገልጹ ነበር፡፡
በአንድ ወቅት በኢራን ፓርላማ ምክትል አፈጉባኤ ሆነው በሚያገለግሉበት ጊዜ የአብዮታዊ ዘቡን ዩኒፎርም በመልበስ በፓርላማው በመገኝት መነጋግሪያ ሆነው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ኢብራሂም ራይሲ ባሸነፉበት በ2021 የኢራን ምርጫ ልብጠጋኙ ሀኪም ለፕሬዝዳንትነት እራሳቸውን እጩ አድርገው አቅርበው የነበረ ቢሆንም ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት እርሳቸው እና ሌሎች እጩዎች ከምርጫ ተሳትፎ ታግደዋል፡፡
የአያቶላዎቹን ጥብቅ ሀይማኖታዊ አስተዳደርን እውቅና እሰጣለሁ የሚሉት ፔዝሽኪያን በኢራን ማህበረሰባዊ ነጻነትን አሰፍናለሁ ብለዋል፡፡
“በሀይማታዊ አስተዳደሩ ጥብቅ የተደረጉ ህጎችን ለማሻሻል እስራለሁ ፣ የኢራንን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተጠቃሚነቷን የሚያረጋግጥ ስትራቴጂን እከተላለሁ፣ የ2015ቱን የኒውክሌር ስምምነት ዳግም ተግባራዊ እንዲሆን በማድረግ በጫና ውስጥ የሚገኝውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ አነቃቃለሁ” የሚሉት ፔዝሽኪያን ለኢራናውያን ቃል የገቧቸው የቤት ስራዎች ናቸው፡፡
ከዚህም ባሻገር በኢራን ያለውን የኢንተርኔት ገደብ እንደሚያላሉና ፖሊሶች ጸጉራቸውን የማይሸፍኑ ሴቶች ላይ የሚወስዱትን ያልተገባ እርምጃ እንደሚቃወሙ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ተናግረው ነበር፡፡