የሳኡዲና ኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቅርቡ በአካል ለመገናኘት ተስማምተዋል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ የረመዳን ፆም መጀመርን አስመልክቶ በስልክ ተወያይተዋል
የሳኡዲና ኢራን በቅርቡ በቻይና ሸምጋይነት የተቋረጠ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለመጀመር መስማማታቸው ይታወሳል
የሳኡዲ አረቢያ የውጭ ጉዳን ሚኒስትር ልኡል ፈይሰል ቢን ፋርሃን አል ሳኡድ እና የኢራን አቻቸው ሆሴን አሚራብደላሂያን በስልክ መወያያታቸው ተነገረ።
የእስልምና እምነት ተከታዮች ቅዱስ ወር የሆነው ረመዳን መጀመሩን አስመልክቶ የተደረገው የስልክ ውይይት በመካከለኛው ምስራቅ የሰላም አየር እንዲነፍስ አድርጓል።
ሚኒስትሮቹ በቅርቡ በአካል ለመገናኘት የተስማሙ ሲሆን፥ የሀገራቱን ኤምባሲዎች በሪያድና በቴህራን ለመክፈት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የሳኡዲ ፕረስ ድርጅት ዘግቧል።
የሱኒ እስልምና አራማጇ ሳኡዲ አረቢያ እና ሺያዋ ኢራን ከየመን እስከ ሶሪያ በእጅ አዙር ሲፋለሙ ቆይተዋል።
ሀገራቱ በተለይም በ2016 ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ካቋረጡ በኋላ በቀጠናው ሃይል መለካካቱን ተያይዘውት እንደነበርም ይታወቃል።
ሳኡዲ የሺያ የሃይማኖት አባትን ገድላለች መባሉ ኢራንን አስቆጥቶ በቴህራን የሚገኘው ኤምባሲዋ በተቃዋሚዎች ከተደበደበ በኋላም የሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መቋረጡ የሚታወስ ነው።
በ2019 በሳኡዲ የነዳጅ ጣቢያዎች ላይ ለተፈፀሙ የሚሳኤልና ድሮን ጥቃቶች ኢራንን ተጠያቂ ያደረገችው ሪያድ ፥ ቴህራን እንደምታስታጥቃቸው የሚነገርላቸውን የሃውቲ አማፂያን የመን ድረስ በመዝለቅ ደብድባለች።
ለሰባት አመታት የዘለቀው በጠላትነት የመተያየት ጊዜ በቻይና ሸምጋይነት ባለፈው ወር በተደረሰ ስምምነት ተቋጭቷል።
ተንታኞች የመካከለኛው ምስራቅ ሃያላኑ ውጥረት ለማርገብና ግንኙነታቸውን ለማደስ መስማማታቸው ለሀገራቱ ብሎም ለቀጠናው ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
ስምምነቱ በኒዩክሌር ፕሮግራሟ ምክንያት ከአሜሪካ ከፍተኛ ጫና የሚደርስባትን ቴህራን ከተጨማሪ መገለል ይታደጋታል፤ ለሪያድም ቀጠናዊ የልማት ተጠቃሚነቷን እንደሚያሳድግላት ይጠበቃል።
ሀገራቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው የጀመሩት ግንኙነትን የማደስ እንቅስቃሴ በቅርቡም በመሪዎች ደረጃ እንደሚታይ ነው የሚጠበቀው።