በኳታር የቱርክ ጦር መኖሩ ቀጣናውን እንደሚያተራምስ ዩኤኢ አስታወቀች
በናጎርኖ ካራባክ ጦርነት አዘርባጃንን የምትደግፈው ቱርክ ሶሪያውያን ወታደሮችን ማዝመቷም ተገልጿል
ቱርክ በተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የምታደርገው ወታደራዊ ጣልቃ ብዙ ሀገራትን አስቆጥቷል
በኳታር የቱርክ ጦር መኖሩ ቀጣናውን እንደሚያተራምስ ዩኤኢ አስታወቀች
ቱርክ በቋታር ጦሯን ማስፈሯ ለባህረ-ሰላጤው ቀጣና ያለመረጋጋት ምንጭ ከመሆኑም ባለፈ ለከፍተኛ መከፋፈል የሚዳርግ መሆኑን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከፍተኛ ተናግረዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አንዋር ጋርጋሽ “በአረብ ባህረ ሰላጤ ውስጥ የቱርክ ወታደራዊ ኃይል መገኘቱ ድንገተኛ ነው” ብለዋል፡፡
ጋርጋሽ አክለውም “የቱርክ ጦር መኖር መገፋፋትን የሚያጠናክር ፣ የቀጣናውን ሉዓላዊነት እና የባህረ-ሰላጤው ሀገሮችን እና የህዝቦቻቸውን ፍላጎት ከግምት ውስጥ የማያስገባም ነው” ማለታቸውን ዘ ናሺናል ዘግቧል፡፡
ሐሙስ ዕለት የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን የቱርክ ወታደሮች በኳታር መኖራቸውን አረጋግጠዋል፡፡
“የቱርክ ወታደሮች በኳታር መገኘታቸው ለኳታር ብቻ ሳይሆን የባህረ-ሰላጤውን አካባቢ ሰላምና መረጋጋትም ለማረጋገጥ ነው” ሲሉ ኤርዶጋን መግለጻቸውም ነው የተዘገበው፡፡
ቱርክ እ.ኤ.አ. በ 2015 ከኳታር ጋር የፀጥታ ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን ከ2017 ጀምሮ ደግሞ ወታሮቿን ማስፈር ጀምራለች፡፡ ይህም የሆነው የባህረ ሰላጤው አገራት ሳዑዲ ዓረቢያ ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ባህሬን ከግብፅ ጋር በመሆን በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት እና እንደ ሙስሊም ወንድማማቾች ያሉ አሸባሪ ቡድኖችን በመደገፍ የሚከሷትን ዶሃን ማግለላቸውን ካሳወቁ በኋላ ነው፡፡
ምንም እንኳን የቱርክ እርምጃ በቀጣናው ሀገራት እንደስጋት ቢታይም ኤርዶጋን “ሁከት ለማሰራጨት ከሚፈልጉ በስተቀር” ኳታር ውስጥ በቱርክ ወታደራዊ ተሳትፎ ማንም ወገን ሊረበሽ አይገባም ብለዋል፡፡
ባለፈው ህዳር ወር የደህንነት ስምምነት አካል የሆነ በዶሃ አቅራቢያ አንድ የቱርክ ወታደራዊ ካምፕ የተገነባ ሲሆን ካምፑ ወደ 5,000 የሚጠጉ ወታደሮችን ያስተናግዳል ነው የተባለው፡፡
ቱርክ በሰሜን ኢራቅ ፣ በሶሪያ እና በሊቢያ የእርስ በእርስ ጦርነቶችም በምታደርጋቸው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቶች እና መሰል ድርጊቶቿ ምዕራባዊያንን እና የአረብ መንግስታትን አስቆጥታለች፡፡
በአርሜኒያ እና በአዘርባጃን መካከል በሚደረገው የናጎርኖ-ካራባክ ጦርነትም በርካታ ሶሪያውያንን መልምላ በአዘርባጃብ ወገን እንዲዋጉ ማሰለፏ ይነገራል፡፡ ዘ ናሺናል ያናገራቸው አንዳንድ ሶሪያውያን ወታደሮች ቱርክ ገንዘብ ከፍላቸው በርካታ ሶሪያውያን በጦርነቱ መሳተፋቸውን እና አላስፈላጊ ጦርነት ውስጥ መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡ በርካታ ሶሪያውያን ወታደሮች መገደላቸውንም የገለጹ ሲሆን ብዙዎች ጦርነቱን ትተው እየተመለሱ መሆኑንም ዘገባው እደሚያመለክተው፡፡