ኡጋንዳ የሀገሪቱ ዳኛ በእስራኤል ላይ የተላለፈውን ውሳኔ መቃወመቻው “አቋሜን አያንጸባርቅም” አለች
እስራኤል በደቡብ አፍሪካ ከሳሽነት ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ቀርባ እንደተወሰነባት ይታወቃል
የኡጋንዳ ዳኛ በዓለም የፍትህ ፍርድ ቤት በእስራኤል ላይ የተላለፈውን ውሳኔ የተቃወሙ ብቸኛ ዳኛ ናቸው
ኡጋንዳ በአለም የፍትህ ፍርድ ቤት ሀገሪቱን የወከሉት ዳኛ በእስራኤል ላይ የተላለፈውን ውሳኔ መቃወማቸው አቋሟን እንደማያሳይ አስታወቀች።
አለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ባሳለፍነው አርብ ደቡብ አፍሪካ በእስራኤል ላይ ያቀረበችውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ ተመልክቶ ብይን መስጠቱ የሚታወስ ሲሆን፤ የኡጋንዳ ዳኛ ውሳኔውን በመቃወም አስተያየት ሰጥተዋል።
ከ17 ዳኞች ፍርድ ቤቱ ያሳለፋቸውን ስድስት ውሳኔዎች በመቃወም ድምጽ የሰጡት የኡጋንዳ ዳኛ ጁሊያ ሴቡቲንዴ ብቻ ናቸው።
ይህንን ተከትሎም የኡጋንዳ መንግስት በሰጠው መግለጫ “ዳኛ ሴቡቲንዴ የወሰዱት እርምጃ የግላቸው አቋም እና አስተያየት ነው እንጂ በምንም መልኩ የኡጋንዳ መንግስት አቋምን አያሳይም” ብሏል።
ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ኡጋዳ በእስራኤል ሃማስ ጦርነት ላይ የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ በኢንቴቤ ጉባዔ ያዘውን አቋም እንምትደግፍም አስታውቋል።
የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ በኡጋዳ ኢንቴቤ ጉባዔው እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ እና የንጹኃን ግድያን በማውገዝ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ ማቀረቡ ይታወሳል።
እስራኤል በጋዛ እየወሰደች ያለውን እርምጃ በቀዳሚነት ከተቃወሙ ሀገራት አንዷ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ አሁንወደ ተመድ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ማቅናቷ ይታወሳል።
በዚህም “እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍሊስጤማውያን ላይ የዘር ፍጅት እየፈጸመች ነው” ያለችው ደቡብ አፍሪካ፤ ሀገሪቱንም በበዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ከሳለች።
ደቡብ አፍሪካ ለፍርድ ቤቱ ባስገባችው ክስ እስራኤል በጋዛ የሃማስ ቡድን ላይ በወሰደችው እርምጃ በ1948 በወጣው የዘር ማጥፋት ስምምነት የተጣለባትን ግዴታ እየጣሰች መሆኗን ገለጻች።
በሀገራት መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን የሚያስተናግደው ከፍተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፍርድ ቤት ደቡብ አፍሪካ በእስራኤል ላይ ባቀረበችው ክስ ላይ በትናናው እለት ብይን ሰጥቷል።
ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ከሃማስ ታጣቂዎች ጋር ጦርነት በምታደርግበት ወቅት የዘር ማጥፋት ድርጊቶችን ለመከላከል እርምጃ እንድትወስድ ያዘዘ ሲሆን፤ ነገር ግን አፋጣኝ የተኩስ አቁም ጥሪ አላቀረበም።