ሳኡዲ ታዋቂው የፊልም ሙዚቃ አቀናባሪ ሃንስ ዚመር አዲስ የብሔራዊ መዝሙር እንዲያዘጋጅላት ጠየቀች
የኦስካር አሸናፊው ሀንስ ዚመር “ዘ ላዮን ኪንግ” እና “ግላድያተር” የተሰኙ ፊልሞችን ማጀቢያ ሙዚቃ አዘጋጅቷል
ሪያድ ስፖርትና ሲኒማን ጨምሮ በተለያዩ የመዝናኛ ዘርፎች በሰፊው እየተሳተፈች ነው
ሳኡዲ አረብያ ታዋቂውን የኦስካር አሸናፊ የፊልም ሙዚቃ አቀናባሪ ሀንስ ዚመር አዲስ ብሔራዊ መዝሙር እንዲያዘጋጅላት ጠየቀች፡፡
የሳውዲ አረቢያ የጠቅላላ መዝናኛ ባለስልጣን ሊቀመንበር ቱርኪ አላሺክ ከዚመር ጋር የተነሱትን ምስል በኤክስ ገጻቸው ባጋሩበት ወቅት “ከዚመር ጋር ለሳውዲ ብሔራዊ መዝሙር አዲስ ቅንብር ማዘጋጀትን ጨምሮ በተለያዩ ግዙፍ የመዝናኛ ፕሮጀክቶች ላይ ተወያይተናል” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ስለሳኡዲ የሚያወሳ “አረቢያ” የተሰኘ ሙዚቃ ለመስራት እና በመጪዎቹ አመታት በሪያድ ትልቅ ኮንሰርት ለማዘጋጀት መወያየታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም “በያርሙክ” ጦርነት እና በካሊድ ቢን አል-ወሊድ ህይወት ላይ ተመስርቶ ለተሰራው ፊልም የማጀቢያ ሙዚቃውን በማቀናበር እንደሚሳተፍ ነው ሊቀመንበሩ የተናገሩት፡፡
በቅርቡ በቃል ደረጃ በተስማሙባቸው የመዝናኛ ፕሮጀክቶች ላይ የመጨረሻ ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ መግለጻቸውን ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡
አዲስ ብሔራዊ መዝሙር እንዲያዘጋጅ የተጠየቀው ሀንስ ዚመር በ1995 “ዘ ላዮን ኪንግ” በ2022 “ዱን” በተሰኘው ፊልም በሰራቸው ሙዚቃዎች ኦስካርን አሸንፏል።
እንዲሁም “ግላዲያተር”፣ “ሬይን ማን” እና “ባትማን ዘ ዳርክ ናይት” ፊልሞችን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸውን ፊልሞች ሙዚቃ ሰርቷል።
"አሽ አል-ማሊክ" ("ንጉሱ ለዘላለም ይኑር") የተሰኘው የሀገሪቱ ብሔራዊ መዝሙር በሳኡዲ አረብያ ንጉሳዊ አስተዳደር መስራች ንጉስ አቡዱላዚዝ ጠያቂነት በግብጻዊው አቀናባሪ በ1947 ነበር የተጻፈው።
ሳውዲ አረቢያ ስፖርት እና ሲኒማን ጨምሮ በተለያዩ የመዝናኛ ዘርፎች በሰፊው እየተሳተፈች ነው፤ ታዋቂ ስፖርታዊ ውድድሮችንም እያስተናገድች ትገኛለች።
ሪያድ የ2034ቱን የአለም ዋንጫ ለማዘጋጀት መመረጧም በመዝናኛው ዘርፍ ገጽታዋን ይበልጥ ለአለም ለማሳየት እንድትጠቀምበት ያግዛታል ተብሎ ይጠበቃል።፡