በሳዑዲ የሚመራው ጥምር ኃይል “በሰንዓ አየር ማረፊያ” ላይ የአየር ጥቃት አደረሰ
የአየር ማረፊያው “ድንበር ዘለል ጥቃቶችን ለመፈጸም አገልግሎት ላይ እየዋለ ነበር”ም ነው የተባለው
በሳዑዲ የሚመራው ጥምር ኃይል “በሰንዓ አየር ማረፊያ” ላይ የአየር ጥቃት አደረሰ
በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምር ኃይል በየመን መዲና ሰንዓ አየር ማረፊያ ላይ የአየር ጥቃት ማድረሱ ተገልጿል፡፡
ጥምር ኃይሉ የአየር ማረፊያው ዒላማ ያደረገበት ምክንያት “ድንበር ዘለል ጥቃቶችን ለመፈጸም አገልግሎት ላይ እየዋለ ነው” በሚል እንደሆነ አስታውቋል።
አየር ማረፊያው ለበርካታ ዓመታት በሁቲ አማጽያን ኃይሎች ቁጥጥር ስር የቆየና የተባበሩት መንግሥታት ለሚመራው የሰብዓዊ አገልግሎት ማዕከል ሆኖ ሲያገለግል የነበረ ነው።
ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ ሰራተኞች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ጥምር ኃይሉ ማሳሰቡንም ነው ሮይተርስ የሳዑዲ መንግሥት ሚዲያን ዋቢ በማድረግ የዘገበው።
የጥምር ኃይሉ ቃለ አቀባዩ ብርጋዴር ጀነራል ቱርኪ አል-ማልኪ ፤ጥቃቱ ወታደራዊ ዒላማ ናቸው ተብለው በሚቆጠሩ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑም ገልጿል።
“የድሮኖች መነሻ ስፍራዎች፣ ድሮኖችን የሚያንቀሳቅሱ ሰራተኞች ማሰልጠኛ፣ እና የድሮኖች ማከማቻ ስፍራዎች” የጥቃቱ ዋና ዋና ዒላማዎች ነበሩም ብሏል ቃለ አቀባዩ ብርጋዴር ጀነራል ቱርኪ አል-ማልኪ፡፡
ጥቃቶቹ በአውሮፕላን ማረፊያው የሥራ ማስኬድ አቅም ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ አይኖራቸውም ብሏል፡፡
በዓረቡ ዓለም ዘንድ በድህነቷ የምትታወቀው የመን ፤ከፈረንጆቹ 2014 ጀምሮ በእስላማዊ አማጺያን እና በመንግሥት መካከል የእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች የምትገኝ ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡
እንደፈረንጆቹ 2015 የሁቲ አማጽያን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውን መንግሥት ከሰንዓ ማስወገዳቸውንና በሳዑዲ የሚመራ ጥምር ጦር በየመን ጣልቃ መግባቱን ተከተሎም “የየመን ጉዳይ በተፎካካሪ የቀጣናው ኃይሎች መካከል የሚደረግ የውክልና ጦርነት” ሆኗል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ውጊያ መባባሱ ደግሞ የየመን ጉዳይ አስከፊ እየሆነ መጥቷል፡፡