የምዕራባውያን ድጋፍ መዘግየት የመልሶ ማጥቃት ዘመቻውን አጓቶታል - ዜለንስኪ
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት በጦር መሳሪያ አቅርቦት ችግር የመልሶ ማጥቃቱ በፍጥነት መቀጠል አለመቻሉን ገልጸዋል
ሞስኮ በዋግነር አመጽ ምክንያት ገታ ያደረገችውን ጦርነት አጠናክራ ልትገፋበት እንደምትችል ይጠበቃል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ምዕራባውያን በፍጥነት የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠየቁ።
ፕሬዝዳንቱ ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የጦር መሳሪያ ድጋፉ መዘግየት የመልሶ ማጥቃት ዘመቻውን እንዳጓተተው አንስተዋል።
የመልሶ ማጥቃቱ በፍጥነት ካልተጀመረ ዩክሬን ተጨማሪ ግዛቷን ማጣቷ እንደማይቀር በመጥቀስም በከፊል በተጀመረው ዘመቻ ኬቭ የገጠማትን ፈተና አብራርተዋል።
ዩክሬን በደቡብ እና ምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍሎች በሩሲያ የተያዙባትን አካባቢዎች ለማስመለስ ዝግጅቷን መጨረሷን ደጋግማ ብትጠቅስም በቂ የጦር መሳሪያ ክምችት እንደሌላት የሚያሳብቅ አስተያየታቸውን ነው ዜለንስኪ የሰጡት።
ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ ከምዕራባውያን ቃል የተገባላቸው የጦር መሳሪያ ድጋፍ በፍጥነት እየደረሰ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት ለዩክሬን እያደረጉት ስላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዩክሬን በተለይም ክፍተት ያለበትን የአየር ሃይሏን ለማደራጀት የአሜሪካ ሰራሹ ኤፍ - 16 ጄቶች እንዲሰጧት ስታቀርበው የነበረው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወሳል።
የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችም ሆነ የኤፍ - 16 ተዋጊ ጄቶች ግን እስካሁን ኬቭ አልደረሱም።
ዜለንስኪ ለእስካሁኑ ድጋፍ ወዳጆቻቸውን አመስግነው አሁንም ቃል የተገቡ የጦር መሳሪያ ድጋፎች ካልደረሱ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻው ይበልጥ መጓተቱ እንደማይቀር ነው ያነሱት።
ሞስኮ በዋግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን አመጽ ምክንያት ገታ ያደረገችውን ጦርነት ዳግም አጠናክራ ልትገፋበት እንደምትችል ይጠበቃል።