ሳዑዲ አረቢያ አሉባልታን በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የሚያሰራጩ ሰዎችን በእስር ቀጣለሁ አለች
ውሳኔው ከሙዚቃ ድግስ ጋር ተያይዞ በወጣት ሴቶች ላይ ትንኮሳ ደርሷል የሚል ዜና መሰራጨቱን ተከትሎ የመጣ ነው
መሰረተ ቢስ መረጃዎችን የሚያሰራጩ ሰዎች እስከ 5 ዓመት የሚደርስ እስርና ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት ይጠብቀቸዋል ተብሏል
ሳዑዲ አረቢያ መሰረተ ቢስ አሉባልታዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የሚያሰራጩ ሰዎችን እንደመትቀጣ የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
በዚህ ተግባር ላይ የተገኙ ሰዎችም እስከ 5 ዓመት የሚደርስ የእስር እና ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት እንደሚጠብቃቸውም ነው ሀገሪቱ ያስታወቀችው።
ሳዑዲ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው አንድ የሙዚቃ ድግስ መሰረዙን ተከትሎ ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ያሉ ወጣት ሴቶች ትንኮሳ እየደረሰባቸው ነው የሚል ዜና ኢንተርኔት ላይ ከተሰራጨ በኋላ ነው።
አንዳንድ ሴቶች በዚህ የሙዚቃ ድግስ ላይ የተፈጠረውን ነገር ለመናገር እንደሚፈሩ ተናረዋል ሲልም ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።
የሳዑዲ አረቢያ የመዝናኛ ዘርፍ ኃላፊዎች ሴቶቹ ያቀረቡትን ቅሬታ በትዊተር ገጻቸው ላይ በተደጋጋሚ እየተረቡ ውድቅ ማድረጋቸውም ተነግሯል።
የኬ-ፖፕ የሙዚቃ ባንድ የሆኑት ስትሬይ ኪድስ ባለፈው ሳምንት ሊያቀርቡ የነበረው የሙዚቃ ድግስ የተሰረዘው በከባድ ነፋስ ምክንያት ነው።
በዚህ የተበሳጩ የሙዚቀኞቹ አድናቂዎች ከሪያድ ወጣ ብሎ ከሚገኘው የድግስ ስፍራ ወደ ቤታቸው ለመመለስ እክል ገጥሟቸው የነበረ ሲሆን፤ አንዳንድሴቶችም በዚሁ ጊዜ ትንኮሳ እንደደረሰባቸው ተነግሯል።
በሌላ በኩል በርካታ በስፍራው ነበርን ያሉ ሰዎች ደግሞ ምንም ነገር አልተፈጠረም ሲሉ የተናሩ ሲሆን፤ የሳዑዲ የመዝናኛ ባለሥልጣን ኃላፊ ተርኪ አል-ሸይኽ በትዊተር ገጻቸው የሴቶቹን አቤቱታ የሚያጣጥል ተደጋጋሚ መልዕክት ጽፈዋል።
ይህንን ተከትሎም የሳዑዲ መንግስት ከእውነት የራቁ አሉባታዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ የሚያሰራጩ ሰዎች ከድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነ እስከ 5 ዓመት የሚደርስ እስር እና ከበድ ያለ የገነዝብ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ያለው።