ተማሪዎችን በ50 ደቂቃ ውስጥ 400 ፑሽአፕ በማሰራት የቀጡት አሰልጣኝ ተከሰሱ
ጥፋታቸው እየተቆጠረ ለአንድ ስህተት 16 ፑሽአፕ የተቀጡት ተማሪዎች ታመው ሆስፒታል ገብተዋል
አሰልጣኙ ግን ቅጣቱ ተጫዋቾቹን በስነምግባር የሚያንጽና አካላዊ ጥንካሬ የሚጨምር እንጂ የሚያስከስስ አይደለም በሚል ይከራከራሉ
በቴክሳስ የሚገኝ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእግርኳስ ቡድን አባላቱን የሚቀጣበት መንገድ አነጋጋሪ ሆኗል።
የ"ሮክወል ሄልዝ" ትምህርትቤት የእግርኳስ ቡድን አሰልጣኙ ጆን ሃሬል እና ረዳቶቻቸው ባለፈው አመት ፈጽመውታል የተባለው የማረሚያ ቅጣት ለክስ ዳርጓቸዋል።
አሰልጣኙ ለተማሪዎቹ ተጫዋቾች የ50 ደቂቃ ስልጠና ሲሰጡ ለአንድ ጥፋት 16 ፑሽአፕ ያሰራሉ።
እያንዳንዱ ጥፋት እየተቆጠረ ቆይቶ 23 ጥፋት የተገኘባቸው 368 ፑሽአፕ እንዲሰሩ ተደርጓል ይላል ከተማሪዎቹ ወላጆች በአንዱ የተመሰረተው ክስ።
በቅጣቱ ምክንያት ከ12 በላይ ሰልጣኝ ተማሪዎች ሆስፒታል የገቡ ሲሆን፥ በሂደት በተደረጉ ምርመራዎችም 26 ተጫዋቾች የጡንቻ ህብረ ህዋስ እንዲሰባበር እና ከደም ጋር እንዲቀላቀል የሚያደርገው "rhabdomyolysis" የተባለ በሽታ ምልክት እንደታየባቸው ተረጋግጧል።
ተማሪዎቹን ከአንድ ሳምንት በላይ በሆስፒታል ውስጥ ያስቆየው ህመም በፍጥነት ባይደረስበት ለኩላሊት እና ልብ ህመም ብሎም ለሞት ይዳርግ ነበር ተብሏል።
የቀረበው ክስ አሰልጣኙ "ጥፋት" ናቸው ብለው ከዘረዘሯቸው ጉዳዮች መካከል የተሳሳተ አለባበስ፣ ከአሰልጣኛና የቡድን አጋር ጋር መልካም ያልሆነ ግንኙነት፣ ስድብና ማንጓጠጥ፣ ኳስ ለማግኘት አለመትጋት የሚሉት ይገኙበታል።
የ"ሮክወል ሄልዝ" ትምህርት ቤት አሰልጣኝ ጆን ሃሬል ተማሪዎችን ሲያሰለጥኑ ማንኛውንም አካላዊ ቅጣት እንዳይወስዱ ማስጠንቀቁንና አሻፈረኝ ብለው መቀጠላቸውን ገልጿል።
ሃሬል ከአወዛጋቢው የቅጣት እርምጃቸው ዜና መውጣት ከሁለት ሳምንት በኋላ ስራቸውን ለቀዋል።
ቅጣቱ ተጫዋቾቹን በስነምግባር ለማነጽ ብሎም አካላዊ ጥንካሬያቸውን ለማሳደግ ያገዘ ነው በሚልም ይከራከራሉ።
400 የሚጠጋ ፑሽአፕ እንዲሰሩ ተገደው ታመው ሆስፒታል ከገቡት ውስጥ አብዛኞቹን ወላጆቻቸው ክስ እንዳይመሰርቱ ሲያግባቡና ሲያስፈራሩ እንደነበር መረጃዎች መገኘታቸውንም ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።