የጸረ ተባይ ኬሚካሎች መካንነትን እንደሚያስከትሉ ተመራማሪዎች አስጠነቀቁ
በመዋቢያ ምርቶች ውስጥ የሚገኙ ኬሚካሎች ለአዕምሮ እና ስነ ተዋልዶ ጤና እክሎች ያደርሳሉ ተብሏል
ተመራማሪዎቹ ኬሚካሎች የአዕምሮ መስነፍንም እንደሚያደርሱ ገልጸዋል
የጸረ ተባይ ኬሚካሎች መካንነትን እንደሚያስከትሉ ተመራማሪዎች አስጠነቀቁ፡፡
የሰው ልጆች ህይወትን ቀለል ለማድረግ በሚል የሚጠቀማቸው የኬሚካል ምርቶች ለከፋ የጤና ችግሮች እንደሚዳርጉ ተገልጿል፡፡
በሀርቫርድ ዩንቨርሲቲ የጀነቲክ ፕሮፌሰር የሆኑት ሞኒካ ኮላይኮቮ እንዳሉት በቤት ውስጥ ያሉ ተባዮችን እና ነፍሳትን ለማጥፋት የምንጠቀማቸው ጸረ ተባይ ኬሚካሎች መካንነትን ያስከትላሉ ብለዋል፡፡
በኬሚካሎቹ ውስጥ ያለው ዲት በሚል የሚጠራው ንጥረ ነገር ዋነኛው ጎጂ ምርት ሲሆን ይህ ምርት ነፍሳት ወይም ተባዮች ከተደበቁበት እንዲወጡ የሚያደርግ ነው፡፡
ተመራማሪዎች እነዚህን ተባዮች በቀላሉ ለመግደል በሚል በኬሚካል ውስጥ የሚጨምሩት ዲት የተሰኘው ንጥረ ነገር በምግብ እና መጠጥ መንገዶች ወደ ሰው ልጆች አካል ሲገባ ብዙ ጉዳቶች እንደሚያደርስ ተመራማሪዋ መናገራቸውን አይ ሳይንስ የተሰኘው የምርምር ጆርናል ዘግቧል፡፡
ይህ ኬሚካልም የሰው ልጅ ስነ ተዋልዶ ጤናን በመጉዳት መካንነት እንዲፈጠር አልያም የተጸነሰው ጽንስ የአዕምሮ ጤና ጉድለት እንዲኖርበት ያደርጋልም ብለዋል፡፡
ዲት የተሰኘው ይህ መርዛማ ንጥረ ነገር ከጸረ ተባይ መድሃኒቶች በተጨማሪ በመዋቢያ ምርቶች ላይም የሚገኝ በመሆኑ ሰዎች ምርቶቹን ሲገዙ እንዲጠነቀቁም ተመራማሪዋ አሳስበዋል፡፡
በተለይም በቆዳ ላይ የሚቀቡ ምርቶች፣ ሽቶ እና ተያያዥ ምርቶች ሲገዙ በምርቶቹ ላይ ያሉ ንጥረ ነገሮችን በማንበብ አነስተኛ ኬሚካ ይዘት ያላቸውን ምርቶች መግዛት ይገባልም ተብሏል፡፡
በመዋቢያ ምርቶች ላይ ያሉ ኬሚካሎች ይዘት መብዛት ለአዕምሮ ስራ መስተጓጎል፣ ጡንቻ አልታዘዝ ማለት፣ ለልብ መድከም እና ተያያዥ ችግሮች ሊዳርግ እንደሚችልም ተመራማሪዋ ገልጸዋል፡፡
ዲት የተሰኘው ንጥረ ነገር ለሁሉም ሰው ጉዳት ያለው ቢሆንም ነፍሰ ጡሮች በእርግዝና ወቅት ከኬሚካል ምርቶች ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲቀንሱ ተመራማሪዋ አሳስበዋል፡፡
ኬሚካሎች የሰው ልጆች አፈጣጠር ወይም ጅን ላይ ለውጦች እንዲመጡ ተጽዕኖ በማድረግ የሚታወቁ በመሆኑ ምርቶቹ ጋር ያሉ ግንኙነቶችን መቀነስ እና በጥንቃቄ መጠቀም ይገባል ተብሏል፡፡