የእስራኤል ተመራማሪዎች የወንድ ልጅ መካንነትን ሊፈታ የሚችል ፈጠራ ማግኘታቸውን ገለጹ
አዲሱ ግኝት በወንድ የዘር ፍሬ መጠን ማነስ ምክንያት ለሚፈጠር መካንነት መፍትሔ እንደሚሆን ተገልጿል
በጨረር ህክምና ምክንያት ለመካንነት የተጋለጡ ወንዶችም ልጅ ወልዶ መሳም እንዲችሉ ያደርጋልም ተብሏል
የእስራኤል ተመራማሪዎች የወንድ ልጅ መካንነትን ሊፈታ የሚችል ፈጠራ ማግኘታቸውን ገለጹ፡፡
የእስራኤል ተመራማሪዎች ለወንዴ የዘር ፍሬ መመረት ምክንያት የሆነ ግኝታቸውን በቤተ ሙከራ መስራታቸውን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ ተመራማሪዎቹ የሰሩት ግኝት አዲስ ፈጠራ ሲሆን በወንድ የዘር ፍሬ መጠን መቀነስ ምክንያት ልጅ ወልደው መሳም ላልቻሉ ሰዎች መፍትሔ ይሆናል ተብሏል፡፡
በዓለም ላይ ካሉ የወንዶች መካንነት ምክንያቶች ውስጥ ቆለጥ ወይም የዘር ፍሬ ከረጢት በቂ የወንድ የዘር ፍሬ መጠን ማመንጨት አለመቻል ዋነኛው ሲሆን አዲሱ ፈጠራ ይህንን ሊፈታ እንደሚችል ተገልጿል፡፡
ሰው ሰራሽ ቆለጥ የተባለው አዲሱ የእስራኤል ተመራማሪዎች ፈጠራ እስካሁን ካሉት የመካንነት ህክምና የተሻለ መፍትሔ ያመጣልም ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አዲሱ ፈጠራ በቀጣይ የወንድ የዘር ፍሬን በቤተ ሙከራ ማልማት እንደሚቻል ፍንጭ የሰጠ እንደሆነም የጥናቱ መሪ እና በባር ኢልሀም ዩንቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ኒትዛን ጎነን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም በልጅነታቸው በካንሰር ህመም ተጠቅተው ነገር ግን በተደጋጋሚ በወሰዱት የጨረር ህክምና ምክንያት ለመካንነት የተዳረጉ ሰዎች ልጅ እንዲወልዱ የማድረግ እድሉ ከፍተኛ ነውም ተብሏል፡፡
የዓለማችን ተመራማሪዎች ሰው ሰራሽ ሳምባ፣ ኩላሊት፣ ጉበት እና ልብን በቤተ ሙከራ መስራታቸውን ከዚህ በፊት ያሳወቁ ሲሆን ወደ በጎ ፈቃደኛ ሰዎች ላይ ለመግጠም ተጨማሪ ምርምሮችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡