የካንሰር ህዋስን 99 በመቶ መግደል የሚያስችል ግኝት ማግኘታቸውን ተመራማሪዎች ገለጹ
አዲሱ ግኝት የብዙዎችን ህይወት ሊታደግ እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል
በዓለማችን በየዓመቱ 10 ሚሊዮን ሰዎች በካንሰር ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ
የካንሰር ህዋስን 99 በመቶ መግደል የሚያስችል ግኝት ማግኘታቸውን ተመራማሪዎች ገለጹ፡፡
በዓለማችን በሕመም ምክንያት ከሚከሰቱ 10 የሰው ልጅ ሞቶች ውስጥ ስድስቱ በካንሰር እንደሚሞቱ የዓለም ጤና ድርጅት ያስረዳል፡፡
ይህ የጤና እክል ሳይባባስ ከታወቀ በሚደረጉ ተከታታይ ህክምናዎች መዳን ቢቻልም ብዙዎቹ ግን የካንሰር መጠኑ ከተባባሰ በኋላ ወደ ህክምና ተቋማት እየመጡ መሆኑ በካንሰር የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር እንዲጨምር አድርጎታል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የጤና ተመራማሪዎች ለካንሰር ፈዋሽ መድሃኒት ለመስራት በየጊዜው ለውጦች ቢኖሩም እስካሁን ግን በፈዋሽነቱ የተረጋገጠ መድሃኒት አልተገኘም፡፡
የአሜሪካ ተመራማሪዎች የካንሰር ህዋስን 99 በመቶ መግደል መቻሉን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
ተመራማሪዎቹ በቤተ ሙከራ ውስጥ አደረግነው ባሉት ጥረት ካንሰር ህዋስ ይገኝበታል በተባለው ስፍራ ላይ ሀይል በኢንፍራሬድ በማስገባት እና በአካባቢው ማዕበል እንዲከሰት በማድረግ የካንሰር ህወሱን መግደል ተችሏል ብለዋል፡፡
በአሜሪካ ሪስ ዩንቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ሲሰሮን አይላ ኦሮዝኮ ለዩሮ ኒውስ እንዳሉት የካንሰር ህዋስን መግደል እንደሚቻል አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
ተመራማሪዋ አክለውም ከእንግዲህ ዋናው ጉዳይ የሚሆነው ይህን በማዕበል የካንሰር ህዋስን የመግደል ግኝት ለሰው ልጆች ህክምና በሚሆን መልኩ ወደ መድሃኒትነት የመቀየሩ ስራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
እንደተመራማሪዋ ገለጻ የካንሰር መድሃኒት የመስራት ስራው ግኝቱ ሊያደርስ የሚችለው የጎንዮሽ ጉዳት ከተጠና በኋላ በመሆኑ ከ10 እስከ 15 ዓመት ሊፈጅ እንደሚችልም ተገልጿል፡፡
ከዚህ በፊት በተደረጉት ምርምሮች የካንሰር መድሃኒትን መስራት ትልቁ ፈተና የካንሰር ህዋሳት በቶሎ መድሃኒቶችን የመቋቋም አቅም ማዳበራቸው እንደነበርም ተመራማሪዋ ተናግረዋል፡፡
የካንስር ህክምና በየጊዜው እየተሸሻለ የመጣ ቢሆንም የሳንባ፣ ጣፊያ እና ጡት ካንሰር አይነቶች ከሌሎች አንጻር ገዳይነታቸው ከፍተኛ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የተለያዩ የካንሰር አይነቶች የሚከሰቱ ቢሆንም የማህጸን በር እና ጡት ካንሰር በአንጻራዊነት ብዙ ዜጎችን እየገደሉ ሲሆን በየጊዜው የህክምና ክትትል አለማድረግ ደግሞ የሟቾችን ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከዚህ በፊት መግለጹ ይታወሳል፡፡