በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል 2ኛው የሰላም ውይይት ተጀምሯል፤ጦርነቱም ቀጥሏል
አሜሪካን ጨምሮ ምእራባውያን ሀገራት የአየር ክልላቸውን ለሩሲያ ዝግ አድርገዋል
ሩሲያ ኪቭን ለመቆጣጠር በማሰብ ግዙፍ ጦር ወደ ኪቭ ግዛት እያስጠጋች ነው
ግጭቱን በሰላም ለመፍታት የሚካሄደው ሁለተኛው ንግግር በሁለቱ ሀገራት ልኡካን መካከል መካሄድ መጀመሩን የሩሲያ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡የመጀመሪያው ንግግር ለሩሲያ አጋር በሆነችው ቤላሩስ መካሄዱ ይታወሳል፡፡
የሰላም ጥረቱ ቢጀመርም ሩሲያ የዩክሬንን ዋና ከተማ ኪቭን ለመቆጣጠር በማለም ግዙፍ ጦር ወደ ኪቭ ግዛት እያስጠጋች መሆኑን የሩሲያን መከላከያ ሚኒስቴር ጠቅሶ አርቲ ዘግቧል፡፡
የሩሲያ እስካሁን ባካሄደችው ዘመቻ በደቡብዊ ዩክሬን የምትገኝው ኬርሶን ከተማ ጨምሮ በርካታ ቦታዎችን መቆጣጠር ችላለች፡፡ የሩሲያ ወታራዊ ዘመቻ በምእራበውያን ዘንድ ያልተወደደ በመሆኑ በርካታ የኢኮኖሚ ማእቀቦች ጎርፍ እየወረደባት ነው፡፡ ምእራባውያን የኢኮኖሚ ማእቀብ ከመጣል በተጨማሪ የአየር ክልላቸውን ለሩሲያ ዝግ አድርገዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ በትናንትናው እለት ባደረገው ስብሰባ ሩሲያ ዩክሬንን መዉረሯን የሚያወግዘዉን የዉሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡
የውሳኔ ሀሳቡ በ143 የድጋፍ ድምጽ፣35 ተአቅቦ እና በ5 ተቃውሞ ሩሲያ ከዩክሬን ለቃ እንድትወጣና ተኩስ እንድታቆም የሚያስጠነቅቀዉን የዉሳኔ ሀሳብ አጸድቋል።ቻይና እና ህንድ ድምጸ ተአቅቦ ካሰሙ ሀገራት ውስጥ ናቸው።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት የከፈተችው፣የኔቶ ጦር ዩክሬንን ጨምሮ ወደ ቀድሞ የሶቬት ህብረት ሀገራት እተሰፋፋ ነው፤ይህም ለደህንነቷ አስጊ እንደሚሆን በመግለጽ ነበር።
ከተጀመረ አንድ ሳምንት ባስቆጠረው ጦርነት፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዩክሬናውያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል። የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት እደቀጠለ ቢሆንም ሀገራቱ ችግሩን ለመፍታት ሁለተኛ ውይይታቸውን ጀምረዋል።