ለወንጀለኞች አዲስ ፊት የሚሰጡት የፊሊፒንስ ሚስጢራዊ ሆስፒታሎች
ከውጭ ሲመለከቷቸው መደበኛ አገልግሎት የሚሰጡ የሚመስሉት ሆስፒታሎች በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን “ፍጹም የተለየ መልክ” በማላበስ ስራ ተሰማርተው ተገኝተዋል
የፊሊፒንስ ፖሊስ የፊት ቀዶ ህክምናና የጸጉር ንቅለ ተከላ አገልግሎት የሚሰጡት ሚስጢራዊ ሆስፒታሎች በቅርቡ እንደሚዘጉ ገልጿል
ፊሊፒንስ በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አዲስ መልክ በማላበስ የተሰማሩ ሁለት ሚስጢራዊ ሆስፒታሎችን በፍተሻ ደርሼባቸዋለሁ አለች።
ሆስፒታሎቹ ከውጭ ሲያዩቸው መደበኛ አገልግሎት የሚሰጡ ይመስላሉ።
ውስጣቸው ግን በሌሎች ሆስፒታሎች የማይገኙ ውድ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚገኙባቸው ናቸው።
የጸጉር ንቅለ ተከላ፣ የጥርስ ማስተካከያ፣ የፊት ቆዳ ቀለምን የሚያነጡ እና ሌሎች ዘመናዊ መሳሪያዎች የተሟሉላቸው ሆስፒታሎች ከሁለት ወራት በፊት ነው በፖሊስ ፍተሻ የተደረገባቸው።
በመዲናዋ ማኒላ ደቡባዊ ክፍል እና ፓሳይ በተባለችው ከተማ የሚገኙት ሆስፒታሎች “ፍጹም የተለየና አዲስ መልክ ያለው ሰውን የሚፈጥሩ ናቸው” ብለዋል የፓኪስታን የተቀነባበሩ ወንጀሎች መከላከል ኮሚሽን ቃል አቀባይ ዊንስተን ጆን ካሲዮ።
ህገወጥ ሆስፒታሎቹ የማንም መታወቂያ ሳይጠይቁ የፊት ቀዶ ህክምና እና ሌሎች አገልግሎቶችን እንደሚሰጡ በምርመራ መረጋገጡንም አብራርተዋል።
ሁለቱ ህገወጥ ሆስፒታሎች በፓሳይ ከተማ ከሚገኘው ሆስፒታል በአራት እጥፍ ሰፊ ናቸው ያሉት ቃል አቀባዩ፥ ደንበኞቻቸው አብዛኞቹ ፊሊፒንስ በህግ በከለከለችው የኦንላይን ውርርድ የተሰማሩ ናቸው ብለዋል።
ፊሊፒንስ በሀገሪቱ ውስጥ የኦንላይን ውርርዶችን ማካሄድ ብትከለክልም አገልግሎቱን ከሀገሪቱ ውጭ ለሚገኙ ደንበኞቻቸው ለሚያቀርቡ ድርጅቶች ግን ፈቃድ ትሰጣለች።
ይህን ፈቃድ እንደ ሽፋን በመጠቀም በስልክ የሚፈጸሙ የማጭበርበር ድርጊቶች እና የሰዎች እገታ ላይ የሚሰማሩ አካላት መኖራቸውን የፊሊፒንስ ፖሊስ ይገልጻል።
እነዚህ በህገወጥ ተግባር የተሰማሩ አካላት በቁጥጥር ስር እንዳይውሉ አዲስ ፊት ይሰጣሉ የተባሉት ሆስፒታሎች በቅርቡ ይዘጋሉ ተብሏል።
በፊሊፒንስ የኦንላይን ውርርድ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ሮድሪጎ ዱቴርቴ የስልጣን ዘመን ተስፋፍቶ እንደነበር የቢቢሲ መረጃ ያወሳል።
በ2022 ዱቴርቴን የተኩት የወቅቱ ፕሬዝዳንት ፈርዲናንድ ማርኮስ ጁኒየር ግን “የኦንላይን ማጭበርበር ማዕከል” የሚል ተቀጽላ የተሰጣትን ሀገራቸውን ስም ለማደስ ዘመቻ መጀመራቸው ነው የሚነገረው።