ኢትዮጵያ ከሱዳን ጦርነት ጋር በተያያዘ ለ18 ሀገራት የበረራ ፈቃድ መስጠቷን ገለጸች
ፈረንሳይ፣ አሜሪካ እና ስፔን ብዙ የበረራ ፈቃድ በኢትዮጵያ የተሰጣቸው ሀገራት ናቸው
በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያዊን ብዙ በመሆናቸው ምክንያት ሁሉንም መርዳት እንዳልቻለችም አስታውቃለች
ኢትዮጵያ ከሱዳን ጦርነት ጋር በተያያዘ ለ18 ሀገራት የበረራ ፈቃድ መስጠቷን ገለጸች።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል ።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ከሱዳን ጦርነት ጋር በተያያዘ ዜጎቻቸውን ከካርቱም ለማስወጣት በሚል የአየር ክልሏን ፈቅዳለች ብለዋል።
እስካሁን ባሉት ጊዜያትም ለ18 ሀገራት 75 የበረራ ፈቃድ እንደሰጠች የገለጹት ቃል አቀባዩ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ እና ስፔን በአንጻራዊነት ብዙ የበረራ ፈቃድ የተሰጣቸው ሀገራት ናቸው ብለዋል።
በሱዳን ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ለመርዳት በካርቱም እና ገዳሪፍ ያሉ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች እየሰሩ እንደሆነም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል ።
ይሁንና በሱዳን ያሉ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ መሆኑ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ሁሉ መርዳት አዳጋች እንሳደረገው አምባሳደር መለስ አክለዋል።
አምባሳደር መለስ እንዳሉት የሱዳን ጦርነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያን መጉዳት ስለማይቀር ጉዳቶችን ለመቀነስ 11 አባላት ያሉት ኮሚቴ መዋቀሩን ተናግረዋል ።
ከፌደራል መንግሥት እና ከክልል ተቋማት የተውጣጣው ይህ ብሔራዊ ኮሚቴ የደህንነት ስጋቶችን መቀነስ፣ አገልግሎቶችን ማቀላጠፍ እና ሌሎች ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
እስካሁን ባሉት ቀናት ውስጥም በኩርሙክ እና መተማ ድንበሮች የውጭ ሀገር ዜጎችን እና ኢትዮጵያዊያንን እየተቀበለ እያስተናገደ ነውም ተብሏል።
የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት ፓስፖርት መያዝ እና የጉዞ ሰነድ ያልያዙ ዜጎችን ከማግኘት ውጪ የተለየ ክስተት እንዳልተከሰተ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።