ለነገው ሃገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊነት በሳታላይት እና ድሮን ቴክኖሎጂ የታገዘ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ
ዝግጅቱ በቴክኖሎጂ ድጋፍ ለተለዩና ለሚከሰቱ አደጋዎች ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል
“ለሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ቀን በቂ ዝግጅት ተደርጓል”- ጠ/ሚ ዐቢይ
መንግሥት ነገ ለሚካሄደው ምርጫ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ደሕንነት ስትራቴጂ ማዘዣ፤ ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ድምፃቸውን ለመስጠት እንዲንቀሳቀሱ የተደረገውን የመጨረሻ ዝግጁነት ለመገምገም፣ ዛሬ መምከሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
“ለሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ቀን በቂ ዝግጅት ተደርጓል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም ዜጎች ነገ ድምፃቸውን ለመስጠት ሲወጡ አካባቢያቸውን በንቃት እንዲከታተሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጸጥታ ዘርፉ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሰማራ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ድጋፍ ለተለዩ እና ለሚከሰቱ አደጋዎች ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት ሰፊ ሥራ መሰራቱንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የገለጹት፡፡
በማዕከላዊ ዕዝ የሁኔታ ክትትል ክፍል ውስጥ ይፋ የተደረገው የብሔራዊ መረጃና ደህንንነት አገልግሎት የምርጫ ደህንነት መድረክ በምርጫ ደህንነት ዘርፍ የተከናወነውን ዝግጁነት አጉልቶ ያሳያል ብሏል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት።
የደህንነቱ ዝግጁነት በሁሉም የሀገሪቱ ማእዘናት ላይ አካላዊ ኃይል ማሰማራትን እንዲሁም የሳይበር ደህንነት ማሻሻያዎችን የተመለከቱ ስጋቶችን ማክሸፍን ያጠቃልላልም ብሏል።
በመላው የፌዴራል እና የክልል ማዘዣ ጣቢያዎች ባሉ የመረጃ መጋራት መሳሪያዎች፣ የሳተላይት ቁጥጥር ስርዓቶች እና የድሮን ቴክኖሎጂ ለዚሁ ዝግጅት መሰማራታቸውንም ነው ጽህፈት ቤቱ ያስታወቀው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን አዲስ አካሄድና ከብሔራዊ ቁልፍ ተግባራት ቀድሞ ብሔራዊ ደህንነትን በማረጋገጥ ረገድ የተፈጠረውን አቅም ተመልክተዋልም ብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ተኛው አገራዊ ምርጫ ማጠቃለያን አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረበው የትብብር ጥያቄ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ፣ ተጠባባቂ የህግ አስፈጻሚ ኃይል ስምሪት መጠየቁ የሚታወስ ነው፡፡