ሰለሞን የ3 ሺህ ሜትር የወንዶች ፍጻሜን አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል
አትሌት ሰለሞን ባረጋ ለኢትዮጵያ ሶስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኘ።
ሰለሞን በሰርቢያ ዋና ከተማ ቤልግሬድ በመካሄድ ላይ ባለው 18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ3 ሺ ሜትር የወንዶች የፍጻሜ ውድድርን በማሸነፍ ነው የወርቅ ሜዳሊያውን ያሸነፈው፡፡
ይህም ኢትዮጵያ በውድድሩ ያገኘችው ሶስተኛ ወርቅ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ሰለሞን ከደቂቃዎች በፊት የተጠናቀቀውን ውድድር 7 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ ከ38 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት አሸንፏል፡፡ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ለሜቻ ግርማ ደግሞ ሰለሞንን ተከትሎ 7፡41፡63 በመግባት ሁለተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያን አግኝቷል፡፡
የዩናይትድ ኪንግደሙ ማርክ ስኮት ደግሞ በ7፡42፡02 ሶስተኛ ሆኗል።
የነ ሰለሞንን ማሸነፍ ተከትሎ ኢትዮጵያ የሻምፒዮናውን የሜዳሊያ ሰንጠረዥ በሶስት ወርቅ፣ በሁለት ብር እና በሁለት ነሐስ በድምሩ በሰባት ሜዳሊያዎች በአንደኛነት እየመራች ነው።
የ18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመጨረሻ ቀን ውድድሮች በመካሄድ ላይ ናቸው። በሻምፒዮናው የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የፍጻሜ ውድድሮች ዛሬ ምሽት ይካሄዳሉ ።
ከምሽቱ 2 ሰአት ከ5 ደቂቃ ላይ በ800 ሜትር ሴቶች አትሌት ሃብታም አለሙ እና አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ።
ከምሽቱ 2 ሰአት ከ30 ደቂቃ በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች አትሌት ሳሙኤል ተፈራና አትሌት ታደሰ ለሚ ይሳተፋሉ።
ትናንት ማምሻውን በተካሄደ የ1 ሺ 500 ሜትር የሴቶች የፍጻሜ ውድድር ጉዳፍ ጸጋይ፣ አክሱማዊት እምባዬ እና ሂሩት መሸሻ በቅደም ተከተል ተከታትለው በመግባት ወርቅ፣ ብር እና ነሃስ ማስገኘታቸው ይታወሳል፡፡