የግብጽን ጥቅም ለማስከበር ጉቦ ተቀብለዋል የተባሉት አሜሪካዊው ሴናተር የ11 ዓመት እስር ተላለፈባቸው
ሴናተር ቦብ ሜኔንዴዝ ለረጅም ዓመታት በአሜሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው ነበሩ
ሴናተሩ ከህዳሴው ግድብ ጋር በተገናኘ የግብጽን ጥቅም እንዲያስከብሩ እና በሌሎች ጉዳዮች ከ600 ሺህ ዶላር በላይ ሙስና ወስደዋል በሚል ክስ ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል
የግብጽን ጥቅም ለማስከበር ጉቦ ተቀብለዋል የተባሉት አሜሪካዊው ሴናተር የ11 ዓመት እስር ተላለፈባቸው።
ባለፉት 40 ዓመታት በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ የነበሩት ቦብ ሜነንዴዝ ለዓመታት የሀገሪቱ ውጭ ግንኙነት ስራዎች ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰውም ነበሩ፡፡
የዘር ሀረጋቸው ከኩባ የሚመዘዘው ሜኔንዴዝ ዲሞክራት ፓርቲን ወክለው የአሜሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤትን ከመቀላቀላቸው በፊት የኒው ጀርሲዋ ዩኒየን ሲቲን በከንቲባነት መርተዋል፡፡
እኝህ ጉምቱ ፖለቲከኛ በፈረንጆቹ 2020 ላይ የወቅቱ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሶስትዮሽ ድርድር ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጫና አድርገዋል ተብሏል፡፡
እንደ ሲኤንኤን ዘገባ ከሆነ ፖለቲከኛው ይህን ያደረጉት ከግብጽ ባለስልጣናት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ጉቦ ከተቀበሉ በኋላ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መሪዎች በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሶስትዮሽ ውይይት በማድረግ ላይ የነበሩ ሲሆን የወቅቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህ ውይይት ወደ ዋሸንግተን እንዲመጣ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡
በዋሸንግተን በተደረጉት ተከታታይ የሶስትዮሽ ድርድር ላይ ኢትዮጵያ በጫና ወደ ስምምነት እንድትመጣ ግፊት ሲደረግ እንደነበር እና ኢትዮጵያ ስምምነቱን አልፈርምም በሚል አቋሟ መጽናቷን በወቅቱ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መግለጫ አውጥቶም ነበር፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ፖለቲከኛው ከግብጽ እና ኳታር ኩባንያዎች ጋር ያልተገባ ጥቅም ትስስር በመፍጠር 150 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ወርቅ እና ከ450 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ ተከፍሏቸዋል የተባለ ሲሆን የሀገሪቱ ፍትህ ተቋማት ባደረጉት ምርመራ ሜኔንዴዝ በጉቦ መቀበል፣ በፍትህ ማዛባት እና ሌሎችም ወንጀሎች ክስ ተመስርቶባቸው በክርክር ላይ ቆይተዋል፡፡
ቦም ሜኔንዴዝ የተመሰረተባቸውን ክስ አምነዋል የተባለ ሲሆን እድሜያቸውን፣ አስቀድሞ አስተዳድራዊ ቅጣቶች እንደተላለፈባቸው እና ሌሎች ምክንያቶችን ታሳቢ አድርጎ ቅጣቱን እንዲቀንስላቸው በጠበቃቸው በኩል ጠይቀዋል።
የሀገሪቱ አቃቢ ህግ በቦብ ሜኔንዴዝ ላይ የ15 ዓመት እስር እንዲተላለፍባቸው ፍርድ ቤቱን የጠየቁ ሲሆን ፍርድ ቤቱም በሴናተሩ ላይ በ11 ዓመት እስር እንዲቀጡ ወስኗል ተብሏል።