ኮሎምቢያ አሜሪካ በግዳጅ ያስወጣቻቸውን ስደተኞች አልቀበልም ማለቷን ተከትሎ የ25 በመቶ ቀረጥ ተጣለባት
አሜሪካ በሁለት ወታደራዊ አውሮፕላኖች የኮሎምቢያ ስደተኞችን በማጓጓዝ ላይ እያለች አውሮፕላኖቹ እንዳያርፉ ተከልክለዋል
ኮሎምቢያ ቡና እና ነዳጅን ጨምሮ በርካታ ምርቶቿን ለአሜሪካ ገበያ በማቅረብ ላይ ነበረች
ኮሎምቢያ አሜሪካ በግዳጅ ያስወጣቻቸውን ስደተኞች አልቀበልም ማለቷን ተከትሎ የ25 በመቶ ቀረጥ ተጣለባት።
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገሯ የገቡ ስደተኞችን በግዳጅ ማባረር ጀምራለች።
አዲሱ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር ስደተኞችን ወደየመጡባቸው ሀገራት በግዳጅ እየመለሰ ሲሆን በትናንትናው ዕለትም የኮሎምቢያ ስደተኞችን ወደ ቦጎታ ለመመለስ ሞክሯል።
በሁለት ወታደራዊ አውሮፕላኖች ስደተኞችን ጭኖ እያጓጓዘ የነበረው የዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር ኮሎምቢያ አውሮፕላኖቹ እንዳያርፉ መከልከሏን ቢቢሲ ዘግቧል።
ይህን ተከትሎም አሜሪካ ከኮሎምቢያ ወደ ሀገሯ በሚገቡ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ቀረጥ ክፍያን ጥላለች።
ከዚህ በተጨማሪም ለኮሎምቢያ ባለስልጣናት ተሰጥተው የነበሩ ቪዛዎች እንዲሰረዙም ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።
ኮሎምቢያ ከአሜሪካ ጋር አለመተባበሯ ከቀጠለ የንግድ ቀረጥ ክፍያው ወደ 50 በመቶ ከፍ ሊል እንደሚችልም ተገልጿል።
የኮሎምቢያ ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ በበኩላቸው ሀገራቸው በአሜሪካ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎችን ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ገልጸው እንደወንጀለኛ ክብራቸውን ባልጠበቀ መልኩ በወታደራዊ አውሮፕላን እንዲመጡ አንፈልግም ብለዋል።
እንዲሁም ኮሎምቢ በአሜሪካ ለተጣለባት ቀረጥ ተመሳሳይ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችልም ፕሬዝዳንት ፔድሮ ተናግረዋል።
አሜሪካ 20 በመቶ የቡና ፍላጎቷን ከኮሎምቢያ የምታስመጣ ሲሆን አቭካዶ፣ ነዳጅ እና ሌሎች አትክልት እና ፍራፍሬዎችንም ከኮሎምቢያ ታስመጣለች።
ዶናልድ ትራምፕ ህገወጥ ስደተኞችን ለመመለስ በማይተባበሩ ሀገራት ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን እንደሚቀጥሉ በተደጋጋሚ ዝተዋል።
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር የአሜሪካ ጎረቤት የሆኑ ሀገራት ህገወጥ ስደተኞች በገፍ ወደ አሜቲካ እንዲገቡ ተባብረዋል የሚል አቋም አለው።
እነዚህን ስደተኞች ወደየመጡበት ሀገራት ለመመለስ ካልተባበሩ የተለያዩ ማዕቀቦች ሊጣልባቸው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።