ሴኔጋል ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ቀዳማዊ እመቤቶች ይኖሯታል
በቅርቡ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያሸነፉት ባሲሩ ዲማዩ ፋየ ዛሬ ቃለ መሀላ ፈጽመው ከሁለት ሚስቶቻቸው ጋር ቤተመንግስት ይገባሉ
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ከአንድ በላይ ሚስት የማግባት ልማድ በስፋት ይታያል
ሴኔጋል በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ቀዳማዊ እመቤቶች ይኖራታል።
አዲሱ የሀገሪቱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ባሲሩ ዲማዩ ፋየ ዛሬ ቃለመሃላ ፈጽመው ወደ ቤተመንግስት የሚገቡት ከሁለት ሚስቶቻቸው ጋር ነው።
የ44 አመቱ ፋየ ከ15 አመት በፊት ካገቧት ማሪያ ሆን አራት ልጆችን ወልደዋል።
አብሳ ፋየንም ባለፈው አመት ማግባታቸውን የሚገልጹት ተመራጩ ፕሬዝዳንት በሁለቱም ሚስቶቻቸው ደስተኛ መሆናቸውን በምርጫ ቅስቀሳቸው ሲገልጹ ተደምጠዋል።
በየምርጫ ቅስቀሳ መድረኩ ከሁለት ሚስቶቻቸው ጋር መታየታቸውም የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት መሳቡና የሴኔጋላውያን መነጋገሪያ ርዕስ እንደነበር ፍራንስ 24 አስታውሷል።
“ከውብ ሚስቶቼ ቆንጆ ልጆች አግኝቻለሁ፤ በጣም ቆንጆዎች ናቸው፤ ሁሌም ከጎኔ ስለሆኑም ፈጣሪዬን በጣም አመሰግነዋለሁ” ሲሉ ነው ፋየ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የተናገሩት።
የአዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ንግግር እና በየአደባባዩ ከሚስቶቻቸው ጋር መታየታቸው ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት ነውር አለመሆኑን ለማመላከት ያለመ ነው ይላሉ ጂቢ ዲያሄት የተባሉ የማህበረሰብ አጥኝ።
በሴኔጋል ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት በተለይ በገጠሪቱ ክፍል የተለመደና ቤተሰብን ለማብዛት አንደኛው መንገድ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
የሀገሪቱ ስታስቱክስ ተቋም በ2013 ያወጣው ጥናትም ከጠቅላላው ጋብቻ 32 ነጥብ 5 በመቶው በዚሁ መንገድ የተከናወነ መሆኑን ያሳያል።
በርካታ ሚስቶችን የማግባቱ ልማድ በሴኔጋላውያን ወንዶች ቢደገፍም ሴቶች ግን ባል ሁሉንም ሚስቶቹን እኩል ማየት ስለማይችል መድልኦ መከሰቱ አይቀርም፤ ጋብቻው ሊታገድ ይገባል ሲሉ ይደመጣል ብሏል የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ በ2022 ባወጣው ሪፖርት።
በ1979 “ሶ ሊንግ ኤ ሌተር” የተሰኘ መጽሃፋቸውን ያሳተሙት ሴኔጋላዊቷ ጸሃፉ ማሪያም ባ በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ ሚስት ማግባትን አጥብቀው ከሚቃወሙት መካከል ይገኙበታል።
ባል ሁለተኛዋን እና ወጣቷን ሚስት መርጠው የመጀመሪያዋን ሲገፏት የሚፈጥረው የብቸኝነት ስሜትና ህመም ከባድ መሆኑን በመጽሃፋቸው አስፍረዋል።
እንደ “ሚስትረስ ኦፍ ኤ ሜሪድ ማን” እና “ፖሊጋሚ” ያሉ የቴሊቪዥን ፕሮግራሞችም በመሰል ጋብቻ ህይወታቸው የተመሳቀለ ሰዎች ታሪክ ይቀርብበታል።
አንዳንድ ሴኔጋላውያን የሚቀርቡ ክሶች ባህልና እምነታችንን የሚቃረን መሆን የለበትም፤ ባል ሚስቶቹን በእኩል እስካየና ትዳሩን መምራት እስከቻለ ድረስ ከአንድ በላይ ሚስት ማግባቱ ሊነቀፍ አይገባም ይላሉ።