መከላከያ፡ አቶ ስብሃት ነጋ በሰርጥ ውስጥ ተደብቀው በቁጥጥር ስር ዋሉ
በትናንትናው እለት አራት የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መደምሰሳቸውን መከላከያ አስታውቆ ነበር
የህወሓት ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ስብሃትና መከላከያን የከዱ የህወሓት ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መከላከያ አስታውቋል
የህወሓት መስራችና ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ስብሃት ነጋ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ
የመከላከያ ሚኒስቴር ስምሪት መምሪያ ኃላፊ ብርጋዴር ጄነራል ተስፋየ አያሌውን ጠቅሶ ኢቢሲ እንደዘገበው አቶ ስብሃት ነጋና ሌሎች የህወሓት አመራሮች መያዛቸውን ዘግቧል፡፡ ብ/ጄነራል ተስፋየ አያሌው እንደገለጹት አቶ ስብሃት ነጋ በቁጥጥር ስር የዋሉት በህወሃት ቡድን አማካኝነት በሰርጥ ውስጥ ተደብቀው ነው ብለዋል፡፡
ብ/ጄነራል ተስፋየ ከስብሃት ነጋ በተጨማሪ ሌሎች የህወሃት አመራሮችና ከመከላከያ የከዱ የህወሃት ቡድን አባላት መያዛቸውን አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ አቶ ስብሃት ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ በመሄድ ህወሓትና እና የፌዴራል መንግስት እሰጥ አገባ ሲገቡ ህወሃትን በመደገፍ ሲከራከሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ስለነበራቸው ሚና እንዲሁም ስለወቅታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካዊ ሁኔታ በሰጡጥ አስተያየት "ህወሓትን የሚተካ የፖለቲካ ኃይል የለም"ማለታቸው ይታወሳል፡፡
በትናንትናው ዕለት የሕወሓት ቃል አቀባይ ሴኩቱሬ ጌታቸው፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ስራ አስኪያጅና የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርአይ አስገዶም፣ የድምጸ ወያኔ ሃላፊ አበበ አስገዶም እና የቀድሞው ክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳንኤል አሰፋ ከነሹፌሮቻቸውና ከጥበቃዎቻቸው ጋር በመከላከያ መደምሰሳቸው መከላከያ ማስታቀቁ መገለጹ ይታወሳል፡፡ እንደተገደሉ ከተጠቀሱት የህወሃት አመራሮች በተጨማሪም 9 የሕወሓት ቁልፍ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ይታወሳል፡፡