ፖለቲካ
መከላከያ ሰራዊትና ፌዴራል ፖሊስ 1000 መስመራዊና ከፍተኛ መኮንኖችን አስለቀቁ
መንግስት በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻውን ማጠናቀቁን አታውቆ ነበር
ከእገታ ከተለቀቁት መካከል የሰሜን እዝ ምክትል አዛዥ ብ/ጄነራል አዳምነህ መንግስቴ ይገኙበታል
የሰሜን ዕዝ ምክትል አዛዥን ብርጋዴር ጀነራል አዳምነህ ጨምሮ በህወሃት ታግተው የነበሩ 1000 ያህል መስመራዊና ከፍተኛ መኮንኖችን ማስለቀቃቸውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት አስታወቀ፡፡
ህወሃት መኮንኖቹን በሸሸበት ቦታ ሁሉ ይዟቸው ሲሸሽ እንደነበር የገለጹት ሜጀር ጀነራል መሐመድ ተሰማ ታግተው የነበረውም ህወሃት በትጥቅ ትግል ወቅት ሲጠቀምበት በነበረ አዴት በተባለ ቦታ ነው ብለዋል፡፡ መኮንኖቹ አሁን በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙና ሰራዊትን መቀላቀላቸውን ገልጸዋል፡፡
መስመራዊና ከፍተኛ መኮንኖች የታገቱት ሕወሓት ጥቅምት 24 ትግራይ ክልል በሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ካደረሰ በኋላ መሆኑን ሜጀር ጀነራል መሀመድ አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መደበኛ የህግ ማስከበር ዘመቻ መጠናቀቁንና ትግራይን መልሶ የመገንባት ስራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡