ፖሊስ ተጠርጣሪውን ይዞ እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ አንድ ግለሰብ በከፈተው ተኩስ ሁለት ግለሰቦች መገደላቸውን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ አስታወቀ፡፡
ትናንት ማታ ከምሽቱ 3 ሰዓት ተኩል አካባቢ በከተማው ቀበሌ 06 ያሬድ ጁስ ቤት ተብሎ በሚጠራው ቦታ አንድ ግለሰብ በከፈተው ተኩስ ሁለት ሰዎች መገደላቸው ሌሎች ደግሞ መቁሰላቸው ተገልጿል፡፡ ድርጊቱን የፈጸመው ግለሰብ ተሰውሮ እንደነበር የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ ገልጿል፡፡
በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ የታክቲክ ወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ደረጀ ነጋ እንደገለፁት ተጠርጣሪው በከፈተው ተኩስ አንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እና አንድ አስተናጋጅ ተገድለዋል፡፡ እንደ ዋና ኢንስፔክተር ደረጀ ገለጻ ተጠርጣሪው ሌሎች ሁለት ሰዎችን አቁስሎ ተሰውሮ የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ ግን ፖሊስ ይዞታል፡፡
ፖሊስ ባደረገው ክትትል ተጠርጣሪው የወጋገን ባንክ ጥበቃ ሰራተኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ተጠርጣሪው ከተደበቀበት ቦታ ከአንድ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃና ከ18 ጥይት ጋር ተይዞ ምርመራ እየተደረገበት ነውም ተብሏል፡፡