በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለስልጣናት በጫካና ዋሻ ለዋሻ ሲንቀሳቀሱ በተደረገ ጠንካራ አሰሳ ነው ተብሏል
የሰሜን ዕዝን በ45 ደቂቃ ውስጥ መብረቃዊ ጥቃት በመፈጸም ከጥቅም ውጭ አድርገነዋል ብሎ የገለፀው የሕወሓት "አፈቀላጤ" ሴኩቱሬ ጌታቸውን ጨምሮ 4 ከፍተኛ የሕወሓት አመራሮች ከነአጃቢዎቻቸውና ጠባቂዎቻቸው መደምሰሳቸውን የመከላከያ ሠራዊት ኃይል ስምሪት መምሪያ ሃላፊ ብርጋዴር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በዚህም መሰረት፣
1. የሕወሓት ቃል አቀባይ ሴኩቱሬ ጌታቸው፣
2. ዘርአይ አስገዶም፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ስራ አስኪያጅና የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበረ፣
3. አበበ አስገዶም፡ የድምጸ ወያኔ ሃላፊ የነበረ፣
4. ዳንኤል አሰፋ፡ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ የነበረ፣ ከሹፌሮቻቸውና ከጥበቃዎቻቸው ጋር በመከላከያ ሠራዊት፣ በፌዴራል የጸጥታ ተቋማትና በትግራይ ህዝብና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በተደረገ የተቀናጀ ዘመቻ መደምሰሳቸውን ብርጋዴል ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው ለኢዜአ ተናግረዋል።
ከተደመሰሱት ውስጥ ሴኩቱሬ ጌታቸው ከዚህ ቀደም በድምጺ ወያነ ቴሌቪዥን በኩል የሕወሓት ኃይል በመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ መብረቃዊ ጥቃት ፈፅሟል ብሎ ማረጋገጡ ይታወሳል።
ከተደመሰሱት በተጨማሪም 9 የሕወሓት ቁልፍ አባላት በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን እነሱም፣
1. ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ፡ የቀድሞ የክልሉ አፈጉባኤ የነበረች፣
2. ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ፡ የቀድሞ የትግራይ ክልል ከተማ ልማት ቢሮ ሃላፊና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ የነበረ፣
3. አቶ ተክለወይኒ አሰፋ፡ የማረት ስራ አስፈጻሚ የነበረ፣
4. አቶ ገብረመድህን ተወልደ፡ የክልሉ ንግድ ቢሮ ሃላፊ የነበረ፣
5. አቶ ወልደጊዮርጊስ ደስታ፡ የክልሉ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ የነበረ፣
6. አምባሳደር አባዲ ዘሙ፡ በሱዳን የኢትዮጵያ የቀድሞ አምባሳደር የነበረና የሕወሓትን ፖለቲካ ክንፍ የተቀላቀለ፣
7. አቶ ቴዎድሮስ ሃጎስ፡ የመለስ አመራር አካዳሚ ፕሬዚዳንትና የኢፈርት ቦርድ ሃላፊ የነበረ፣
8. ወይዘሮ ምህረት ተክላይ፡ የክልሉ ምክር ቤት ህግ አማካሪ የነበረች እንዲሁም
9. አቶ ብርሃነ አደም መሃመድ፡ የክልሉ የንብረትና ግዥ ስራ ሂደት ሃላፊ የነበረ በቁጥጥር ስር የዋሉ ናቸው ተብሏል።
ከላይ የተጠቀሱት የሕወሓት ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር የዋሉት በጫካና ዋሻ ለዋሻ ሲንቀሳቀሱ በተደረገ ጠንካራ አሰሳ መሆኑንም ብርጋዴል ጀኔራሉ ገልጸዋል።