ሰሜን ኮሪያ ያሻሻለችው ህገመንግስት ደቡብ ኮሪያን “ጠላት ሀገር” ሲል በየነ
ፒዮንግያንግ በሀገራቱ ድንበር የሚገኝ መንገድን ካወደመች ከሁለት ቀናት በኋላ ነው ሴኡልን በጠላትነት መፈረጇን ያስታወቀችው
ሴኡል በበኩሏ የጠላትነት ፍረጃውን ለሁለቱ ኮሪያዎች ውህደት የማይበጅ ነው በሚል ተቃውማዋለች
ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ ያሻሻለችው ህገመንግስት ደቡብ ኮሪያን “ጠላት ሀገር” የሚል ብያኔ ሰጥቷታል።
የሰሜን ኮሪያ ፓርላማ ለሁለት ቀናት መክሮበት ተሻሽሏል የተባለው ህገመንግስት ጎረቤት ደቡብ ኮሪያን በጠላት መፈረጁ የኮሪያ ልሳነ ምድርን ውጥረት የሚያባብስ መሆኑ ተነግሯል።
ፒዮንግያንግ በሀገራቱ ድንበር የሚገኝ መንገድን ካወደመች ከሁለት ቀናት በኋላ ነው ሴኡልን በህገመንግስቷ በጠላትነት መፈረጇን ያስታወቀችው።
ብሄራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ (ኬሲኤንኤ) ሁለቱን ሀገራት በሚያገናኘው መንገድና የባቡር መስመር መውደሙ ህገመንግስቱን እንደማክበር የሚቆጠር ነው ብሎታል። ህገመንግስቱ ሴኡልን በጠላትነት መፈረጁን በመጥቀስ።
የደቡብ ኮሪያ የውህደት ሚኒስቴር የፒዮንግያንግን ፍረጃ ለአንድነት እና ውህደት የማይበጅ ነው በሚል ተቃውሞታል።
የደቡብ ኮሪያ መንግስት በፒዮንግያንግ ሊፈጸም ለሚችል ጸብ አጫሪ ድርጊት ፈጣንና ከባድ የኣአጻፋ ምላሽ ይሰጣል ሲልም አስጠንቅቋል ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።
ተንታኞች ኪም ጆንግ ኡን ደቡብ ኮሪያን በውጭ ጠላትነት መፈረጃቸው የኒዩክሌር መሳሪያዎችን ለመጠቀም ህጋዊ ድጋፍ ለማግኘት በማሰብ ሊሆን እንደሚችል ያነሳሉ።
ከአሜሪካ ጋር በደቡብ ኮሪያ በኩል ሳይሆን በቀጥታ ለመደራደርም ሴኡልን “ጠላት ሀገር” አድርገው መበየንን መርጠው ሊሆን ይችላል የሚሉ አሉ።
ሴኡል ግን እርምጃው የኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር ከዚህ ቀደም የወሰዳቸው ሰላማዊ የውህደት ጥረቶችን ያለመፈለግና ጦርነትን አጥብቆ የመሻት ማሳያ ነው ብላዋለች።
የኪም አስተዳደር ባለፉት ወራት የሁለቱን ኮሪያዎች ውህደት የሚያመላክቱ ሀውልቶች እና የሀገራቱን ግንኙነት ለማሻሻል የተቋቋሙ ተቋማት እንዲፈርሱ ማድረጉ ይታወሳል።
ወጣቱ መሪ ባለፈው አመት ጥር ወር ላይ የመልሶ መዋሀድ ፖሊሲው እንዲሰረዝ ማዘዛቸውም አይዘነጋም።