በህመም ላይ የሚገኙትን የሰሜን ኮርያ መሪ ልትተካ የምትችለው የ11 አመት ታዳጊ ማን ናት?
የኪም ጆንግ ኡን የደም ግፊትና ስኳር ህመማቸው እየተባባሰ እንደሚገኝ የደቡብ ኮርያ የሰለላ ተቋም አስታውቋል
አወዛጋቢውን መሪ እንደምትተካ የምትጠበቀው ታዳጊ በሚስጥር የአስተዳደር ስልጠናዎችን እየወሰደች ትገኛለች
የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጤንነት መታወክን ተከትሎ ከእርሳቸው ስልጣኑን በመረከብ ሀገሪቱን ማን ሊያስተዳድራት ይችላል የሚለው ትልቅ ጥያቄን ፈጥሯል፡፡
170 ሴንቲሜትር ቁመት ያላቸውና 140 ኪሎግራም የሚመዝኑት ኪም ያልተመጣጠነ ክብደታቸው ከልክ በላይ የሚወስዱት አልኮልና ሲጋራ ማጨሳቸው የስኳር እና ደም ግፊት በሽታ አስከትሎባቸዋል።
የ40 አመቱ መሪ ከሶስት አመት በፊት አመጋገባቸውን በማስተካከል ክብደታቸውን በእጅጉ መቀነስ ቢችሉም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ክብደታቸው ወደቀድሞው መመለሱን የወጡ ምስሎች አሳይተዋል።
የደቡብ ኮሪያ ዋነኛው የስለላ ተቋም “ኤንአይሲ” በትናንትናው እለት ይፋ ባደረገው መረጃ የኪም ክብደት 140 ኪሎግራም እንደሚገመትና ለከባድ የልብ ህመም የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን አመላክቷል።
ይህን ተከትሎም የእርሳቸውን ቦታ በመተካት የ11 አመቷ ልጃቸው ኪም ጁ-ኤ ፒዮንግያንግን ልታስተዳደር እንደምትችል መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡
“ኤንአይሲ” የተባለው የሴኡል የስለላ ተቋም ባወጣው መረጃ መሰረት ታዳጊዋ የአስተዳደር እና የመሪነት ትምህርቶችን በድብቅ እየወሰደች ትገኛለች፡፡
ሰሜን ኮሪያ እንደ ሀገር ከተመሰረተች ከ1940 ጀምሮ የኪም ቤተሰቦች ሀገሪቷን በተከታታይ የመሩ ሲሆን የ11 አመቷ ኪም ጁ-ኤ ለመጀመርያ ጊዜ በህዝብ ፊት የታየችው ፒዮንግያነግ በ2022 ሁዋሶንግ 17 የተባለውን አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳኤል ሙከራ ባደረገችበት ወቅት ነው፡፡
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከአባቷ ጋር በተለያዩ ወታደራዊ እና ሀገራዊ ሁነቶች ላይ መታየት የጀመረችው ታዳጊ ኪም ካሏቸው ሶስት ልጆች ሁለተኛዋ እንደሆነች ይነገራል፡፡
የሰሜን ኮርያ የመጀመሪያው መሪ ኪም ሱንግ እና ልጃቸው ኪም ጆንግ ኢል ተተኪያቸውን ሲመርጡ በሚስጥራዊ ማሰልጠኛዎች ውስጥ የተለያዩ ትምህርቶችን እንዲወስዱ ያደርጉ እንደነበር የደቡብ ኮርያ የስለላ ተቋም ገልጿል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኪም ካሏቸው ልጆች በተለየ ሁኔታ በተለያዩ ትላልቅ መድረኮች ላይ ከአባቷ ጋር የምትታየው ኪም ጁ-ኤ በተመሳሳይ ተተኪ መሆኗን ለማሳየት እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ስልጠናዎችን እየወሰደች እንደሆነ ደርሸበታለሁ ያለው የስለላ ተቋሙ በሰሜን ኮርያ መገናኛ ብዙሀንም ታዳጊዋን የሚያወዳድሱ የተለያዩ የፕሮፖጋንዳ ዘገባዎች እየተሰራጩ ይገኛሉ ብሏል፡፡
በ40 አመት እድሜ ላይ የሚገኙት የደቡብ ኮሪያ ሶስተኛ መሪ ኪም ጆንግ ኡን የጤና ሁኔታቸው ከተሻሻለ ለሚቀጥሉት አስርተ አመታት ሀገሪቱን የሚያስተዳድሩ ሲሆን የከፋ ሁኔታ ካጋጠማቸው ግን የ11 አመቷ ልጃቸው ስልጣኑን የመረከብ እድሏ ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡