የስዊስ ፍርድ ቤት ሴፕ ብላተር እና ሚሼል ፕላቲኒን ነጻ ሲል አሰናበተ
በአንድ ወቅት የዓለም አቀፍ ስፖርት ኃያላን የነበሩት ግለሰቦቹ ከእግር ኳሱ ዓለም ታግደው መቆየታቸው የሚታወስ ነው
የቀድሞው የፊፋ አለቃ ሴፕ ብላተር እና የአውሮፓ እግር ኳስ ፕሬዝዳንት ሚሼል ፕላቲኒ በማጭበርበር ወንጀል ክስ ላይ እንደነበሩ ይታወቃል
የስዊዘርላንድ ፍርድ ቤት በማጭበርበር ወንጀል ተከሰው የነበሩትን የቀድሞው የዓለም እግር ኳስ (ፊፋ) አለቃ ሴፕ ብላተር እና የአውሮፓ እግር ኳስ ፕሬዝዳንት ሚሼል ፕላቲኒ ነጻ ሲል አሰናበተ፡፡
አዛውንቱ ሴፕ ብላተር ፊፋ ለቀድሞው የፈረንሳይ ኮኮብ ሚሼል ፕላቲኒ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮ አላግባብ እንዲከፍል ሁኔታዎችን አመቻችተዋል በሚል ነበር በፈረንጆቹ 2011 በሙስና ቅሌት የተከሰሱት፡፡
ላለፉት 11 ገደማ ዓመታትም ንጽህናቸውን ለማረጋገጥ ሲከራከሩ ቆይተዋል፡፡ ባሳለፍነው ወር ችሎት ፊት ቀርበው እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡
ክሱ በኃያልነታቸው የሚጠቀሱት ሁለቱም የእግር ኳስ ባለስልጣናት ከስልጣናቸው እንዲለቁ ምክንያት ሆኗል፡፡ ሆኖም ክሱን ያጣጣሉት የ86 ዓመቱ ብላተር ብሩ ለሰጡት የምክር አገልግሎት ለቀድሞው የዩኤፋ ኃላፊ ፕላቲኒ የተከፈለ እንጂ ያለ አግባብ የወጣ እንዳይደለ በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡
ፕላቲኒም በበኩላቸው የተቀበልኩት ገንዘብ ፊፋን ለማማከር የተከፈለ ነው የሚል መከራከሪያ ሲያቀርቡ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡
ብላተር ፊፋን ለ17 አመታት መርተዋል፡፡ ፕላቲኒ ደግሞ እርሳቸውን ተክተው ፊፋን በፕሬዝዳንትነት ይመራሉ ተብሎ ነበር የሚጠበቀው፡፡ ሆኖም ተፈጸመ በተባለው በዚህ የሙስና ቅሌት ምክንያት ሁለቱም ከስልጣን ለመልቀቅ ተገደዋል፡፡
ስልጣን መልቀቅ ብቻም ሳይሆን ከየትኛውም ዐይነት የእግር ኳስ ውድድሮች ታግደው እንዲቆዩ መደረጉም ይታወሳል፡፡
ሲንከባለል ረዥም አመታትን የዘለቀው ክርክር ሂደት ዛሬ አርብ ሃምሌ 1 ቀን 2014 ዓ/ም የመጨረሻው ብይን ተሰጥቶበት እልባት ስለማግኘቱ ተነግሯል፡፡
ዛሬ ሃምሌ 8 (እ.ኤ.አ) ከችሎቱ የተሰየመው የስዊስ ፍርድ ቤት ሴፕ ብላተር እና ሚሼል ፕላቲኒ በሙስና ክስ ጥፋተኛ እንዳልሆኑ በማረጋገጥ ነጻ ሲል አሰናብቷቸዋል።