ፖላንድ “በምንም ስም ቢሆን” ከሩሲያ ጋር መጫወት እንደማትፈልግ ገለጸች
የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) በቀጣይ የምታደርጋቸውን ጨዋታዎች ካለ ሰንደቅ ዓላማ እና ካለብሔራዊ መዝሙር እንድትጫወት ወሰነ።
ፊፋ ውሳኔውን ያስተላለፈው ሩሲያ ዩክሬንን “ወራለች” በመሚል መሆኑም ተገልጿል።
በዚህም መሰረት ሩሲያ ጨዋታዎችን የምታደርገው በገለልተኛ ሜዳ ሲሆን መዝሙሯ በጨዋታዎች ላይ እንዳይዘመር፤ ሰንደቅ ዓላማዋም እንዳይውለበለብ ተወስኗል። ውድድሩን የምታደርገውም በሩሲያ እግር ኳስ ሕብረት ስም ነውም ተብሏል።
እንግሊዝ፣ ዌልስ፣ ፖላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክ እና ስዊድን ከሩሲያ ጋር እግር ካስ አንጫወትም ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ሩሲያ እና ፖላንድ ጨዋታ ያላቸው ቢሆንም ፖላንድ መጫወት እንደማትፈልግ ገልጻ የነበረ ሲሆን ሌሎች ሀገራትም ይህንኑ ተከትለዋል።
ሩሲያ እና ዩክሬን የጀመሩት ጦርነት ዛሬ አምስተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን፤ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሩሲያን እያገለሉ መሆኑን ተገልጿል።
ፊፋ ሩሲያ በገለልተኛ ሜዳ ውድድር እንዲታደርግ ያሳለፈውን ውሳኔ ፖላንድ ተቃውማለች። የፖላንድ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ሴዛሪ ኩሌስዛ የፊፋ ውሳኔ ትክክል አለመሆኑን ጠቅሰዋል። “በምንም ስም ቢሆንም ከሩሲያ ጋር መጫወት አንፈልግም” ሲሉም ነው የተናገሩት።
ስዊድንም በፊፋ ውሳኔ ደስተኛ እንዳልሆነች ገልጻ መልዕክቱን ከፊፋ መቀበሏንና ለዛሬ ምንም አስተያየት እንደሌላት አስታውቃለች።