በጉብኝቱ ወቅትም ዩኤኢ እና ኦስትሪያ የስትራቴጂያዊ ወዳጅነት ስምምነት ተፈራርመዋል
የአቡዳቢ ልዑል አልጋወራሽ እና የተባሩት አረብ ኢሚሬቶች ጦር ኃይሎች ምክትል አዛዥ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ኦስትሪያ ገብተዋል፡፡
ሼክ ቢንዛይድ ቬና አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኦስትሪያው መራሄ መንግስት ሰባስቲያን ኩርዝ አቀባበል እንዳደረጉላቸው ተገልጿል።
አበቀባበሉ ላይም የዩኤኢ እና ኦስትሪያ ጠንካራ ወዳጅነት ውይይት ተደርጎበታል ተብሏል።
የሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን የቬና ጉብኝት የሀገራቱን ግንኑነት የበለጠ ለማጠናከር ያለመ እንደሆነም ነው የተገለጸው።
ሁለቱ መሪዎች በኢኮኖሚ ትብብር፤ በቱሪዝም፤ እና ቀጣይ ጥቅምት በዱባይ በሚካሄደው ኤክስፖ ዙሪያ ተወያይተዋል። በዱባይ ኤክስፖ ኦስትሪያ ተሳታፊ እንደሆነችም ተገልጿል።
ሁለቱ መሪዎች ባደረጉት ውይይት ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች መነሳታቸው ተገልጿል።
የዩኤኢ ኢንዱስትሪ እና ቴክኖሎጅ ሚኒስትር ሱልጣን አል ጃቤር (ዶ/ር) እና የኦስትሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ስቻለንበርግ የስትራቴጂያዊ ወዳጅነት ስምምነት ማድረጋቸውም ተሰምቷል።
ስምምነቱም የአቡዳቢ ልዑል አልጋወራሽ እና የዩኤኢ ጦር ኃይሎች ምክትል አዛዥ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን እና የኦስትሪያው መራሄ መንግስት ሰባስቲያን ኩርዝ በተገኙበት መደረጉ ተገልጿል።