ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ በቫቲካን ፋውንዴሽን የሰብአዊነት ሽልማት ተበረከተላቸው
ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ በዓለም ዙሪያ ለሰሩት የሰብአዊ ድጋፍ ስራ መሸለማቸው ተገልጿል
ዩኤኢ ባለፉት ዓመታት በ135 ሀገራት ያደረገችው የሰብአዊ ድጋፍ ስራ በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ ቀርቧል
የአቡዳቢ ልዑል አልጋወራሽ እና የዩኤኢ ጦር ኃይሎች ምክትል አዛዥ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን የቫቲካን ፋውንዴሽን የሰብአዊነት ሽልማት ተረከቡ።
የሽልማት ርክክብ ስነ ስርዓቱ ትናንት ምሽት በኢሚሬትስ ቤተ መንግስት ውስጥ መካሄዱ ታውቋል።
ሽልማቱንም ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድን በመወከል የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የውጭ ጉዳይ እና ዓለም ቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር ደኤታ ሼክ ሻክቦውት ቢን ናህያን ተቀብለዋል።
ሽልማቱን የቫቲካን የጳጳሳዊ ትምህርት ፋውንዴሽን ፕሬዚዳንት ካርዲናል ጁሴፔ ቭርሳልዲ ናቸው ወደ አቡ ዳቢ በመጓዝ ያበረከቱት።
ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በዓለም ዙሪያ በሰብአዊ ድጋፍ ለሰሩት ስራ በተለይም ኮቪድ 19ን ተከትሎ ለሰሩት የሰብአዊ ድጋፍ ስራ የተበረከተ መሆኑ ተነግሯል።
የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ባለፉት ዓመታት በ135 ሀገራት ያደረገችውን የሰብአዊ ድጋፍ የሚያሳይ ቪዲዮም በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ ቀርቧል።
ከሽልማት ስነ ስርዓቱ ጎን ለጎንም የቫቲካን የጳጳሳዊ ትምህርት ፋውንዴሽን ፕሬዚዳንት ካርዲናል ጁሴፔ ቭርሳልዲ ከዩኤኢ የትምህርት ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ካርዲናል ጁሴፔ ቭርሳልዲ በዚሁ ወቅት ትምህርት ልማትን እና ሰላምን ለማምጣት ወሳኝ እና መሰረታዊ ነገር መሆኑን አንስተዋል።
“ዓለምን ለመለወጥ፤ አሁን ያለውን ስርዓተ ትምህርት መቀየር ያስፈልጋል” የሚለውን የሮማ ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ ንግግርንም አስታውሰዋል።
የሮማ ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 በዩኤኢ የመጀመሪያ ጉብኝት ማድረጋቸው የታወሳል።
በወቅቱም “ዩኤኢ አብሮ የመኖር እና የሰው ልጅ ወንድማማችነት ተምሳሌት ለመሆን እየሞከረች ያለች እና የተለያዩ ስልጣኔዎችና ባህሎች በአንድ ላይ የያዘች መገናኛ ሀገር ናት” ብለው ነበር።